ሞሃመድ ሳላህ የ2017 የአፍሪካ የአመቱ ኮኮብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጹና የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሃመድ ሳላህ የ2017 የአፍሪካ የአመቱ ኮኮብ ተጫዋችነት ሽልማትን አሸነፈ።

ምሽት በጋና ዋና ከተማ አክራ በተካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ምርጫ ሳላህ የክለብ አጋሩ ሳዲዮ ማኔን አስከትሎ ነው አሸናፊ መሆን የቻለው።

የጋቦኑና የጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትመንድ አጥቂ ፒዬር ኤሚሪክ ኦባሜያንግ ደግሞ ሶስተኛ በመሆን ተመርጧል።

ሳላህ ባለፈው ወር የቢቢሲ የአመቱ የአፍሪካ ኮኮብ ተጫዋችነት ሽልማትን ማሸነፉም ይታወሳል።

ሃገሩ ለአለም ዋንጫ ባደረገችው ጉዞም በወሳኞቹ ሰባት ጎሎች ተሳትፎ በማድረግ፥ ከጣሊያኑ የ19 90 የአለም ዋንጫ በኋላ ፈርኦኖቹን ለትልቁ መድረክ አብቅቷቸዋል።

ሳላህ በማጣሪያው አምስት ጎሎችን ሲያስቆጥር ሁለት ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ በማቀበል ባለውለታቸው ነው።

በክለብ ቆይታውም አስደናቂ ጊዜን እያሳላፈ ይገኛል።

ከሽልማቱ በኋላ በሰጠው አስተያየትም የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት ለእርሱ ልዩ እንደነበር ተናግሯል።

ሽልማቱን በማግኘቱም ህልሙን እንዳሳካ የጠቀሰው ሳላህ፥ ሽልማቱን ለመላው አፍሪካውያንና ለግብጽ ህጻናት መታሰቢያ ይሁንልኝ ብሏል።

አፍሪካውያን ህጻናትም በራሳቸው ማመንና የተሻለ ቦታ እንደሚደርሱ ማለምን እንዳያቆሙም መልዕክቱን አስተላልፏል።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ