ሰሜን ኮሪያ የኦሎምፒክ ልኡኳን ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመላክ መወሰኗ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሜን ኮሪያ የኦሎምቲክ ልኡኳን ቡድኗን በደቡብ ኮሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ላይ ለመላክ መስማማቷን ሴኡል አስታወቀች።

ሰሜን ኮሪያ የምትልካቸው የኦሎምፒክ ልኡክ ውስጥም አትሌቶች፣ ድጋፍ ሰጪዎች እና ሌሎችም ሰዎች እንደሚካተቱበት ነው የተነገረው።

ውሳኔው ላይ የተደረሰውም ሁለቱ ሀገራት ከሁለት ዓመታት በኋላ በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ በዛሬው እለት መወያየት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።

ደቡብ ኮሪያ በኦሎምፒክ ጨዋታው ጊዜ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተለያዩ ቤተሰቦችን እንደገና የማገናኘት ስራ ለመስራት ማቀዷን አስታውቃለች።

በዚህ ደረጃ መስማማት መቻል ለሁለቱም ሀገራት በጣም ወሳኝ ነው የተባለ ሲሆን፥ ደቡብ ኮሪያ ሁለቱን ሀገራት ዳግም ግንኙነታቸውን ለማደስ ተከታታይ ውይይቶች እንዲካሄዱ ፍላጎቷ መሆኑ ተነግሯል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በዛሬው እለት በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ የተጀመረው ውይይት የሰላም ቀጠና በምትባለው እና በሁለቱ ሀገራት ድንበር መካከል በሚትገኘዋ ፓንሙንጆም ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።

በውይይቱ ወቅት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የደቡብ ኮሪያው የአንድነት ሚኒስትር ሃዬ ሱንግ፥ ሰሜን ኮሪያ የከፍተኛ ባለስልጣናት ልኡክን ጨምሮ፤ የሀገሪቱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ አትሌቶች፣ ደጋፊዎች፣ ታዛቢዎች፣ የቴክዋንዶ ቡድን እና የጋዜጠኞች ቡድንን ለመላክ ተስማምታለች ብለዋል።

ደቡብ ኮሪያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ወታደራዊ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቧንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ www.bbc.com