ገንዘቤ ዲባባ የስፔን የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር በ1500 ሜትር አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በስፔን ማድሪድ የተካሄደውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር ተካፍላ አሸንፋለች።

ገንዘቤ ዲባባ ትናንት ምሽት የተካሄደውን የ1 ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር 4 ደቂቃ፣ ከ02 ሰከንድ ከ43 ማርክሮ ሰከንድ በመግባት ነው ያሸነፈችው።

ጀርመናዊቷ አትሌት ኮንስታንዜ ክሆልስተር ውድድሩን በሁለተኝነት ስታጠናቅቅ፤ የብሪያኒያዋ አትሌት ኤሊሽ ማክሎጋን 3ኛ፣ ሞሮኳዊቷ ራቤብ አራፊ 4ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያዊቷ አክሱማዊት አምባዬ 5ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

ትናንት ምሽት የተካሄደው የስፔን ማድሪድ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዚህ ዓመት ከሚያካሂዳቸው ስድስት የቤት ውስጥ ውድድሮች ሶስተኛው ነው።

የመጀመሪያው ውድድር ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፥ ሁለተኛውም በሌላዋ የጀርመን ከተማ ዱሲልዶርፍ ከትናንት በስቲያ መካሄዱ ይታወቃል።

ገንዘቤ ዲባባ በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ የ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ 3 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ከ45 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ማሸነፏም የሚታወስ ነው።

ትናንት ምሽት የተካሄደውን የ1 ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ያሸነፈችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ5 ቀናት ውስጥ ሁለተኛ ድሏን ማጣጣም ችላለች።

አትሌት ገንዘቤ በአንድና በ2 ማይል፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር፣ በ3 እና በ5 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ናት።