በቻምፒየንስ ሊጉ ማንቼስተር ሲቲ በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተጀምረዋል።

በጣሊያንና ስዊዘርላንድ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች የእንግሊዝ ክለቦች የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።

ወደ ቱሪን ያቀናው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከጁቬንቱስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል።

ጎንዛሎ ሄጉዌን አሮጊቷን ቀዳሚ ሲያደርግ ሃሪ ኬንና ኤሪክሰን ደግሞ የእንግሊዙን ክለብ አቻ ማድረግ ችለዋል።

ቶተንሃም በኳስ ቁጥጥር የተሻለ በነበረበት ጨዋታ ያስመዘገበው አቻ ውጤት ለመልሱ ጨዋታ የተሻለ እድል እንዲይዝ አድርጎታል።

በሌላ ጨዋታ ወደ ስዊዘርላንድ ያቀናው ማንቼስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ባዜልን 4 ለ 0 በማሸነፍ የሩብ ፍጻሜ ጉዞውን ቀላል አድርጎታል።

ለሲቲ ኢካይ ጉንዶጋን ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር በርናርዶ ሲልቫና ሰርጅዮ አጉዌሮ ደግሞ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል።

ዛሬ በስታዲዮ ድራጋኦ ፖርቶ ሊቨርፑልን ያስተናግዳል።

ሊቨርፑልም ከስምንት አመት በኋላ በቻምፒየንስ ሊጉ የመጀመሪያ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ሲገናኙ ሊቨርፑል ሁለት በማሸነፍና ሁየት አቻ በመለያየት የተሻለ ክብረ ወሰን አለው።

ቀዮቹን አሸንፈው የማያውቁት ፖርቶዎች ባለፉት ሶስት አመታት በዚህ ዙር ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፈዋል።

በሊቨርፑል በኩል አማካዩ ኢምር ካን የማይሰለፍ ሲሆን፥ ፈርሚንሆና ሞሃመድ ሳላህ በእንግሊዙ ክለብ በኩል ይጠበቃሉ።

ቪንሰንት አቡባካር ደግሞ የፖርቹጋሉ ክለብ ተስፋ የሚያደርግበት ተጫዋች ነው።

በሌላ ጨዋታ ከዋክብቶቹን ያሰባሰቡት ሪያልማድሪድና ፒ ኤስ ጂ ምሽት ይጫወታሉ።

ከወቅታዊ አቋም አንጻር የፓሪሱ ክለብ የተሻለ ቢመስልም በሳምንቱ መጨረሻ ሪያል ማድሪድ በሰፊ ጎል ማሸነፉ ለዛሬው ጨዋታ የተሻለ እንዲዘጋጅ ሊረዳው ይችላል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም ፒ ኤስ ጂ በቻምፒየንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ካደረጋቸው ስድስት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎቹ ውስጥ አራቱን በሽንፈት ማጠናቀቁ፥ በአንጻሩ ማድሪድ በሜዳው

ስድስት ጨዋታዎች በዚህ መድረክ ማሸነፉ ግምቱ ወደ ስፔኑ ክለብ እንዲያደላ አድርጎታል።

ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።