በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ ወደ ቀጣይ ዙር እንዲያልፍ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ ሱዳኑ አልሰላም ዋኡ ጋር የመልስ ጨዋታ ሳያደርግ በቀጥታ ወደ ቀጣይ ዙር እንዲያልፍ ተወሰነ።

ባሳለፍነው እሁድ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአልሰላም ዋኡ ጋር ሊያደርገው ታስቦ የነበረው ጨዋታ እንግዳው ቡድን አለመገኘቱ ይታወሳል።

የዕለቱ የጨዋታ ኮሚሽነር ጉዳዩን ለካፍ ካሳወቁ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ለካፍ ካሳወቀ በኋላ ካፍ ዛሬ ከካይሮ ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት የካፍ ኢንተር ክለብ ኮሚቴ በሌላው የደቡብ ሱዳን ቡድን አልሂላል ጁባ እና አል ሰላም ዋኡ ክለብ እንደተሸነፉ ተቆጥሮ ከውድድር እንዲሰረዙ ወስኗል።

ቅዱስ ጊዮርጊስም የመልስ ጨዋታ እንደማይኖረውና በቀጥታ ወደ ቀጣይ ዙር እንዲያልፍ መወሰኑን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።