ለወላይታ ዲቻ ተጨዋቾች የገንዘብ ሽልማት ተበረከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2010(ኤፍ ቢ ሲ)ወላይታ ዲቻ የግብጹ ዛማሊክን ማሸነፉን ተከትሎ የቡድኑ ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር ሽልማት ተበረከተላቸው።

በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ትናንት በተካሄደው የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ የግብጹን ዛማሊክን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።

ወላይታ ዲቻ ማሸነፉን ተከትሎ ክለቡ ከ520 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለእያንዳንዱ ተጫዋች የ20 ሺህ ብር ጉርሻ ማበርከቱን የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ተናግረዋል።

ሁሉቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት አማካኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን፥ ወላይታ ዲቻም ከቴለቭዥን ስርጭት ሽያጭ 25 ሺህ ዶላር ማግኘቱ ተመልክቷል።

ከዚህ በፊት ዲቻ ከሜዳው ውጭ ሲያሸንፍ ለተጨዋቾች 5 ሺህ ጉርሻ ይሰጣቸው እንደነበረ ያስታወሱት ዶክተር ጌታሁን፥ በአሁኑ ወቅት ገንዘቡ ወደ 20 ሺህ ብር ከፍ እንዲል መደረጉን ገልፀዋል።

በግብጽ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ቡድኑ ካሸነፈ ለተጨዋቾች ተመሳሳይ ሽልማት እንደተዘጋጀ ጠቁመው፥ ሽልማቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ወላይታ ዲቻ ትናንት ያሳየው ብቃት ከሳምንት በፊት ከዛንዚባሩ ዙማሙቶ ክለብ ጋር ካደረገው ጫወታ ጋር ሲነጻጸር በኳስ ቁጥጥር፣ ተግባብቶ በመጫወትና በታክቲክ መሻሻል ተስተወሎበታል።

ወላይታ ዲቻ በጫዋታው የበላይነት የወሰደ ሲሆን በርካታ ደጋፊዎች በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተገኝተው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

የግብጹ ዛማሊክ ከተመሰረተ 107 ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን በአንጻሩ ወላይታ ዲቻ ደግሞ በ2005 ዓ.ም የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል።

ወላይታ ዲቻ ከአሥር ቀን በኋላ የመልስ ጨዋታውን ወደ ግብፅ በመሄድ እንደሚያካሂድ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።