የህዳሴው ግድብ ዋንጫ እግር ኳስ ውድድር ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2010(ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ አመት አስመልክቶ የሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታድየም ዛሬ ተጀምሯል።


ዛሬ በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሁለት ለዜሮ አሸንፏል።

በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ሃብታሙ ገዛኸኝ ባስቆጠራት ጎል እንዲሁም ከእረፍት በኋላ መሃመድ አብዱላጢስ ባገባው ጎል ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሁለት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል።

የውድድሩ ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኛል።

የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች በመጪው እሁድ በሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ የሚገናኙ ሲሆን፥ ተሸናፊዎቹ የደረጃ ጨዋታ ያደርጋሉ።

የፍጻሜው ጨዋታ እሁድ ከቀኑ 10 ሰዓት ሲካሄድ የደረጃ ጨዋታው 8፡00 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ውድድሩ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ አዘጋጅተውታል።

የእግር ኳስ ውድድሩ ዋነኛ ዓላማ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያና በግድቡ ዙሪያ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ነው።

ምንጭ፦ኢዜአ