በ30ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 2 ለ1 አሸነፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ30ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ ተከታዩን ሊቨርፑልን 2 ለ1 በማሸነፍ ሁለተኝነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በኦልትራፎርድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ማርከስ ራሽፎርድ ባለሜዳዎቹን አሸናፊ ያደረጉትን ሁለት ጎሎች በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥረዋል።

ሊቨርፑልን ከሽንፈት ያላዳነችውን ግብ የማንችስተሩ ተከላካይ ኤሪክ ቤሊ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል።

በዚህም ማንችስተር ዩናይትድ ነጥቡን ወደ 65 ከፍ በማድረግ የሁለተኝነት ስፍሯን ሲያጠናክር ሊቨር ፑል ደግሞ 60 ነጥብ በመሰብሰብ በነበረበት የሶስተኝነት ደረጃ ተቀምጧል።

በሌላ በኩል በስፔን ላሊጋ በተደረገ አንድ ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ34ኛው እና በ84 ኛው ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው 2 ጎሎች ሪያልማድሪድ አይባርን 2 ለ1 አሸንፏል።