ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታለቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያዘጋጀው 15ኛው ቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሂዷል።

"ከጥቃት ነጻ ህይወት መብቴ ነው" በሚል መሪ መልክት በተካሄደው በዚህ ውድድር 12 ሺህ ሴቶች ተሳትፈውበታል፡፡

ውድድሩን አትሌት ፀሐይ ገመቹ አንደኛ በመውጣት ስታሸንፍ፤ አትሌት ደባሽ ኪላል ከሱር ኮንስትራክሽን ሁለተኛ፣ አትሌት የኔነሽ ጥላሁን ደግሞ ሶስተኛ ወጥተዋል።

ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት አትሌቶች ከ15 ሽህ እስከ 7 ሺህ 500 ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

5k_run_2.jpg

የውድድሩ በየዓመቱ መካሄድ ሴቶችን ከመደገፍ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አትሌት መሰረት ደፋር ገልጻለች።

የተሳታፊዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን የገለጸችው አትሌት መሰረት፥ በቀጣይም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሴቶችን ለማሳተፍ ጥረት ይደረጋል ብላለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፥ ውድድሩ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚናና ተምሳሌትነታቸውን በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብሏል ።

ሴቶች ለአገር እድገትና ልማት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያለው ሃይሌ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ ከወንዶቹ በተሻለ ብዙ ሜዳሊያ የሚያገኙት ሴት አትሌቶች መሆናቸውን ጠቅሷል።

ይህ ደግሞ ሴቶችን ማብቃት ከቻልን ውጤታማ መሆን አንደሚቻል የሚያሳይ እንደሆነ መግለጹን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።