በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ላይ ተካፍለው ድል ቀንቷቸዋል።

ጃፓን ናጎያ በተካሄደው የማራቶን ውድድር አትሌት መስከረም አሰፋ አሸናፊ ሆናለች።

አትሌት መስከረም ውድድሩን ለመጠናቀቅ ሁለት ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ ጊዜ የወሰደባት ሲሆን፥ ኬንያዊቷ ጀሜሊ ቫላሪ እና ጃፓናዊቷ ሴኪኒ ሃናሚ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል 

በጣሊያን ሮም-ኦቲያ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ሀብታምነሽ ሀይሉ እና ዴራ ዲዳ ከኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ድል አድርገዋል።

በተመሳሳይ የወንዶች ውድድር አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ቀዳሚ ሲሆን፤ኬንያውያኑ ሞሰስ ኬሚ እና ጀስተስ ካንጎጎ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ፈፅመዋል።

ስፔን ባርሴሎና በተካሄደው የማራቶን ውድድር ደግሞ በሴቶች ዘርፍ በላይነሽ ፀጋዬ 2ኛ፣ ወርቅነሽ አለሙ 3ኛ፣ አለሚቱ ቤኛ 4ኛ ስፍራን ይዘው ሲያጠናቅቁ፤አንደኛ የወጣቺው ኬንያዊቷ ሩት ቼቢቶክ ነች፡፡

በዚሁ የባርሴሎና የማራቶን ሩጫ ውድድር በወንዶች ኬንያዉያኑ አንቶኑ ማርቲም፣ ሲላስ ቶ እና ኪምሳምቡ ሂላሪ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ቦታ ይዘው በበላይነት አጠናቀዋል።

ኢትየጵያውያኑ አትሌት ታሪኩ ክንፉ 4ኛ፣ ፀጋዬ ከበደ 5ኛ እና ፅዳት አያና 6ኛ ደረጃ ይዘዋል።

በሆላንድ ዴን ሃግ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ገነት ጋሼ በየነ፣ ዘውድነሽ አየለ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሲወጡ፤ ማጃ ንዩንዋንደር ከስዊትዘርላንድ አንድኛ ሆናለች።

በወንዶች ኬንያውያኑ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ስፍራ ይዘው ጨርሰዋል።

ፖርቹጋል ሊስበን ከተማ ላይ በተከናወነው የወንዶች ግማሽ ማራቶን ዮሃንስ ገበረ ጊዮርጊስ ሁለተኛ ወጥቷል፡፡

ኬንያዊው ኤሪክ ኪፕታኑ የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሌላው ኬንያዊ ሞሪስ ሙኔኔ 3ኛው ሆኖ ማጠናቀቁን አፍሪካን አትሌቲክስ ዩናይትድን ጠቅሱ ኢዜአ ዘግቧል።