በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የግብፁን ዛማሌክ ክለብ በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈፉት የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ቡድን አባላት አዲስ አበባ ገቡ።

የወላይታ ድቻ የእግር ኳስ ክለብ አባላት አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የክለቡ ደጋፊዎች እና የስፖርቱ ቤተሰቦች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

dicha_t_t.jpg

ባሳለፍነው እሁድ በካይሮ አል-ሰላም ስታዲየም በተካሄደ የመልስ ጨዋታ 90 ደቂቃውን በዛማሌክ 2 ለ 1 መሪነት በመጠናቀቁ ድምር ውጤቱ 3 አቻ በማለቁ የመለያ ምት ተሰጥቶ ወላይታ ድቻ በመለያ ምት ዛማሌክን ማሸነፉ ይታወሳል።

ወላይታ ድቻ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሃዋሳ አለም ቀአፍ ስታዲየም የግብፁን ዛማሌክን በማስተናገድ 2ለ1 ማሸነፉም ይታወሳል።

ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያም የዛንዚባሩን ዚማሞቶ ክለብን በደርሶ መልስ ውጤት 2ለ1 በመርታት ነበር ከግብፁ ዛማሌክ ጋር የተገናኘው።

የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ የዛንዚባሩን ክለብ ዚማሞቶ ቅድመ ማጣርያ በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍን ተከትሎ ለእያንዳንዱ ተጫዋች የ20 ሺህ ብር የማበረታቻ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎ ነበር።

ክለቡ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታም የግብፁ ዛማሊክን ማሸነፉን ተከትሎ የቡድኑ ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር ሽልማት እንዳበረከተላቸው ይታወሳል።

ወደ ግብፅ በማቅናት ዛማሌከን በማሸነፍ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የገቡት የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶች እንደሚበረከቱላቸው የሚጠበቅ ሲሆን፥ ሶዶ እና ሀዋሳ ላይም ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል ተብሏል።