ቀነኒሳ እሁድ በለንደን ማራቶን ይሮጣል

አዲስአበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እሁድ በሚካሄደው የ38ኛው የለንደን ማራቶን ውድድር ላይ ይሮጣል፡፡

ከቀነኒሳ ጋር ሌላኛው ኢትዮጵያዊው ጉያ አዶላ በውድድሩ ላይ ይሳተፋል፡፡

ጉያ ባለፈው ዓመት በተደረገው የበርሊን ማራቶን በ2 ሰዓት ከዜሮ ሦስት ደቂቃ ከአርባ ስድስት ሰከንድ በመግባት በሁለተኛነት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ሩጫውን 39 ሺህ ሰዎች እንደሚያጠናቅቁት የሚገመት ሲሆን፥ ቀነኒሳ ከአሸናፊዎቹ መካከል ዋነኛው ተጠባቂ ነው ተብሏል፡፡

ቀነኒሳ በለንደን ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው የዱባይና የበርሊን ማራቶኖች ስኬታማ እንዳልነበረ ያነሱለት ሲሆን፥ በፓሪስና በርሊን ከአሸነፈባቸው የማራቶን ውድድሮች በስተቀር በሌሎች ደስተኛ ያለመሆኑን ጠቅሷል፡፡

እንዲሁም መቼና የት እንደሆነ ባይገምትም የማራቶን ሪከርድን በእጁ ማስገባት እንደሚፈልግና እስከአሁን ያለመያዙም እንደሚያበሳጨው ለጋዜጠኞቹ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ገልፆ ለለንደን ማራቶን ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

 የ35 ዓመቱ ቀነኒሳ የዓለም ሁለተኛው ፈጣኑ የማራቶን ሰዓት ባላቤት ሲሆን፥ በሦስት ኦሎምፒክና በአምስት የዓለም ሻምፕዮናዎች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነው፡፡

እሁድ በሚደረገው ውድድር ኢሉድ ኪፕቾጊ እና ሞ ፋራህ የሚሳተፉ ሲሆን፥ ከቀነኒሳ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

 

ምንጭ፦ሌትስረንዶትኮምና ሌሎች
በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ