ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችው ትኩረት ማሳያዎች ናቸው - ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር እና የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችውን ትኩረት ማሳያዎች እንደሆኑ አንዳንድ ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ሳምንት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡት የጉባኤው ተሳታፊዎች በኤሌክትሪክ የሚሰራውን ቀላል ባቡር እና ከመዲናዋ ነዋሪዎች ቤት የሚወጣውን ደረቅ ቆሻሻ የሚጠቀመው የረጲ ኃይል ማመንጫን ጎብኝተዋል።

ግንባታው የተጠናቀቀው የረጲ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አገሪቱ ከብክለት የጸዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለው ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።

የዓለምአቀፉ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሮበርት ዳውሰን፥ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በተግባር ያሳየችባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፥ በመሆኑም አረንጓዴ ልማትን ለማምጣት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው ብለዋል።

“ከከተማዋ የሚወጣውን ደረቅ ቆሻሻ በእንዲህ አይነት ቴክኖሎጂ ወደ ኃይል ምንጭነት መቀየር ደግሞ ቆሻሻን በአግባቡ ከማስወገድ ባለፈ ለከተማዋ ነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው፤” ሲሉም ሮበርት ዳውሰን ገልጸዋል።

የባቡር ትራንስፖርቱም ከብክለት የጸዳ መሆኑ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል።

ከማይናማር የመጡት ዶክተር አሮን ሩዜል በበኩላቸው “ወደ ሌሎች ከተሞች መስፋፋት ያለባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። ለምሳሌ የባቡር መስመሩን ወደ 500 ኪሎ ሜትር ለማስፋፋት መታቀዱ በጣም ጥሩ ነው። ይሄ ደግሞ አገሪቷ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ኢኮኖሚዋን አስተማማኝ እንድታደርግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከኖርዌይ የመጡት ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ ቬዲስ ቪክ ደግሞ “በዚህ በአጭር ጊዜ እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መመልከታችን በጣም አስገራሚ ነው። በተለይም የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ወደ ስራ ሲገባ ለማየት ጓጉቻለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በከተማዋ እየጨመረ ያለውን የህዝብ ቁጥር ሊመጥን የሚችል የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እንደ ረጲ ያሉ ታዳሽ የኃይል አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ጎብኚዎቹ ገልፀዋል።

የከተሞች የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የትራንስፖርት ፍላጎቱም ስለሚጨምር ከሰውም ከአካባቢም ጋር የተላመደ ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢ መሆኑንም ተነግሯል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ