ኢኳዶር ለዊኪሊክስ መስራች ዊሊያም አሳንጅ ዜግነት ሰጠች

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢኳዶር ለዊክሊስ መስራች ዊሊያም አሳንጅ ሙሉ ዜግነት መስጠቷን አስታወቀች።

መረጃ አፈትላኪው አሳንጅ በብሪታኒያ ለንደን የሚገኘው የደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ከ5 ዓመት በላይ በጥገኝነት ኖሯል።

የኢኳዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ፌርናንዳ ኤስፒኖሳ በትናንትናው እለት በኢኳዶር ዋና ከተማ ኩዊቶ በሰጡት መግለጫ፥ የኢኳዶር መንግስት በሀገሪቱ ጥበቃ ስር ለሚገኘው ዊሊያም አሳንጅ ሙሉ ዜግነት መስጠቱን አረጋግጠዋል።

የዊሊያም አሳንጅ ዜግነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሳስ 3 2017 አንስቶ የፀና መሆኑን ያስታወቁት የኢኳዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤስፒኖሳ፥ ከብሪታኒያ መንግስት ጋር ያለበትን ችግር ለመፍታት እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ከቆይታ በኋላ በሰጠው ምላሸም፥ ኢኳዶር ለዊሊያም አሳንጅ ዲፕሎማቲክ እውቅና እንዲሰጠው ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ መደረጉን አስታውቋል።

መረጃ አፈትላኪው አሳንጅ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ በለንደን የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ በጥገኝነት እየኖረ ይገኛል።

ጁሊያን አሳንጅ ስዊድን የተመሰረተበትን የጾታዊ ጥቃት ክስ በመሸሽ ነው ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ በመኖር ላይ የሚገኘው።

የስዊድን አቃቤ ህግ የ45 አመቱ ዊሊያም አሳንጅ ላይ የተከፈተው ክስ ከ7 ዓመት በኋላ ባሳለፍነው ዓመት እንዲዘጋ ማድረጉም ይታወሳል።

ስዊድን ክሱ መቋረጡን ብትገልጽም፤ የብሪታኒያ ፖሊስ ግን ዊሊያም አሳንጅ ከኢኳዶር ኤምባሲ ከወጣ በቁጥጥር ስር እንደሚያውለው እና ለአሜሪካ አሳልፎ እንደሚሰጠው ሲዝት ቆይቷል።

የዊኪሊክስ መስራቹ ዊሊያም አሳንጅ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሰነዶች እንዲያፈተልኩ በማድረጉ አሜሪካ በወንጀል እንደትፈልገው ይታወቃል።

ምንጭ፦ www.presstv.com