በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ የአየር ሁኔታ ያመዝናል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝንባቸው የብሄራዊ የሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው እንዳስታወቀው፥ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በአብዛኛው እየቀነሰ እንደሚሄድ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የአየር ሁኔታው ለፍራፍሬና ለጓሮ አትክልቶች እድገት እንዲሁም ለእንስሳት ስምሪት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛውና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ለጥቂት ቀናት የሚቆይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በዚሁ መሰረት ኢሉ አባቦራ፣ ጅማ፣ አዲስ አበባ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በትግራይ ክልል የደቡብ ዞኖች እና ከአፋር ክልል ዞን ሶስትና አምስት አካባቢዎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ይህ የአየር ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ሰብል በተሰበሰበበትና የበልግ ወቅት ዝግጅት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የአፈር እርጥበት ከማሻሻል አንጻር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ለዕጽዋት ዕድገትና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል እገዛ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

የሰብል ስብሰባው ሙሉ ለሙሉ ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች የሚጠበቀው ዝናብ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኤጀንሲው አሳስቧል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ