በህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ለሚሳተፉ እንግዶች 132 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የሚገኙ 132 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚካሄደው 30ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ከሆቴሎቹ ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የሚኒስቴሩ የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርብ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሆቴሎችን ጥራት የማስጠበቅ የግምገማ ስራ በዘላቂነት እየተከናወነ ነው።

ሆቴሎቹ ጥራት ያለው ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግም በኮከብ ደረጃ ከተለዩት በተጨማሪ አዲስና ደረጃ ያልተሰጣቸውን በማጠቃለል የቅድመ ዝግጅት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

አገልግሎቱን ለመስጠት የሚፈለገውን ደረጃ ያሟላሉ የተባሉት ሆቴሎች ዝርዝርም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተልኳል።

ጉባኤው በሚካሄድበት ወቅት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ በእንግዶች በኩል ቅሬታ ሲቀርብበት መቆየቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመፍታት ከነገ በስቲያ ከሆቴል ባለቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ቀጠሮ መያዙን ጠቁመዋል።

ጉባኤው የሃገር ገፅታ የሚገነባበት፣ ሌሎች ስብሰባዎችና ጎብኝዎችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ሆቴሎች ጥንቃቄ የተሞላበት አገልግሎት እንዲሰጡም አሳስበዋል።

ሆቴሎች በበኩላቸው አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው የእንግዶቻቸውን መምጣት በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የሆቴሎቹ ስራ አስኪያጆች ተናግረዋል።

ሆቴሎቹ በጉባኤ ወቅት የተጋነነ ዋጋ የመጠየቅ ነገር ቢኖርም ከወትሮው ተመሳሳይ የሆነ ዋጋ ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።

ከጥር 14 ቀን እስከ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው 30ኛው የኅብረቱ ጉባኤ የአፍሪካና የሌሎች ሃገራት መሪዎች፣ የአህጉርና ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።