ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለስራ ጉብኝት ወደ ህንድ አምርተዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከነገ ጀምሮ በህንድ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ወደ ህንድ ያቀኑ ሲሆን፥ በህንድ የስድስት ቀናት ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።

ኔታንያሁ ከመረጃ መረብ፣ ከመከላከያና ከግብርናው ዘርፍ የተውጣጡ 130 ልዑካንን አካተው ነው ወደ ህንድ ያመሩት ተብሏል።

በነገው እለትም በሙምባይ ጉብኝት በማድረግ የህንድ ቆይታቸውን ይጀምራሉ ነው የተባለው።

እስራኤል ለህንድ የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥ ግንባር ቀደም እንደሆነች ይነገራል።

ህንድም በመቶ ሚሊየን ዶላሮች የሚገመት ዋጋ ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች ከእስራኤል ትገዛለች።

ህንድ በቅርቡ ከእስራኤል በ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያዘዘችውን ፀረ ሚሳኤልና ፀረ ታንክ መሳሪያ ግዥ ሰርዛለች።

ኔታንያሁም በጉብኝታቸው ከመሳሪያ ግዥው መሰረዝ ጋር በተያያዘ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

ህንድ ግዥውን ብትሰርዝም በ72 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎችን የመግዛት እቅድ እንዳላት የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

ሃገራቱ ከጦር መሳሪያ ሽያጭና ግዥ ባለፈም የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንደሚያደርጉም መረጃዎች ያመላክታሉ።

 


ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ