በድሬዳዋ ከ1 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በድሬዳዋ ከተማ በ350 ሚሊየን ብር ወጪ የ1 ሺህ 50 የጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የከተማው የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ገዛኽኝ ታድዮስ እንደገለጹት፥ የቤቶቹን ግንባታ ሥራ በመጪው የካቲት 2010 ዓ.ም በ30 ሄክታር መሬት ላይ ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል።

"በአሁኑ ወቅትም ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስችሉ የዲዛይን ሥራ፣ የአማካሪ ድርጅት ቅጥር፣ የቦታ ጠረጋ፣ የመጋዘን ግንባታና የመሳሰሉት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል " ብለዋል።

ግንባታውን የሚያከናውኑ 16 ተቋራጭ ድርጅቶችም መለየታቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ገዛኽኝ ገለጻ፥ የሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለሁለት እና ባለአራት ወለል ህንጻ ያላቸው ናቸው።

በቤቶቹ ተጠቃሚ የሚሆን 17 ሺህ ነዋሪዎች ተመዝገበው ከ90 ሚሊየን ብር በላይ መቆጠባቸውንም ተናግረዋል።

በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሥራ በብሎኬት ማምረት፣ በፕሪካስት፣ በበርና መስኮት፣ በጠጠርና ድንጋይ ማምረትና ማቅረብ ሥራ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውም አመልክተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የቤቶቹ ግንባታ ሥራ በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል።

አስተዳደሩ በከተማው የሚስተዋለውን የመኖርያ ቤት እጥረት ለማቃለል ባለፉት 10 ዓመታት ከ3 ሺህ 200 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለ12 ሺህ ነዋሪዎች በእጣ ማከፋፈሉን አስታውሰዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ