ዶ/ር መረራን ጨምሮ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች ከእስር ተለቀቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፌደራል ደረጃ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ እና ክሳቸው የተቋረጠላቸው 115 ተጠርጣሪዎች ከእስር ተለቀቁ።

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።" መባሉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ዛሬ ዶክተር መረራ ጉዲና እና ዶክተር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ 115 ተጠርጣሪዎች ተለቀዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ዶክተር መረራ ጉዲና ይህ እርምጃ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር መንግስት የወሰደው አንድ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።

"መንግስት ሰፊ ድጋፍ ካላቸው የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ሀቀኛ ድርድር በማድረግ ሁላችንንም በእኩል የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ቢያደርግ መልካም ነው" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና አሁን ያለው ጅማሮም ጥሩ መሆኑን ነው ያነሱት።

tibebe_1.jpgtibe_dr_4.jpg

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን  መግለፁ ይታወሳል።

በአራት መስፈርቶች ተለይተው ክሳቸው ከተቋረጠው ተጠርጣሪዎች መካከል 115ቱ በፌደራል ደረጃ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ 413 ደግሞ ከደቡብ ክልል የቀረቡ ናቸው።

ከደቡብ ክልል ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች በክልሉ በጌዲኦ ዞንና በኮንሶ ወረዳ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በመሳተፍ የተጠረጠሩ ናቸው።

በፌደራልና በደቡብ ክልል ቀርበው ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች ውጭ ግን ሌሎች ክልሎች ክሳቸው የሚቋረጥላቸውን ተጠርጣሪዎች ገና በመለየት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የተፈረደባቸው እና በይቅርታ የሚፈቱትን በተመለከተም በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት እየተለዩ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ተናግረው፥ መለየቱ ግን ጊዜ እንደሚወስድ ነው ያስታወቁት።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በተከታታይ እየተጣራ በይቅርታ እንደሚለቀቁ ነው በዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ ያመለከቱት።

 

በተያያዘ በደቡብ ክልል ክሳቸዉ የተቋረጠ ተጠርጣሪዎች መካከል በመጀመሪያው ዙር 361 ሰዎች ዛሬ ከእስር ተለቀዋል።

የደቡብ ክለል ፍትህ ቢሮ እንዳስታወቀው፥ በጌዲዮ ዞን በሁከትና ብጥብጥ በመሳተፍ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 502 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ነው 361 ሰዎች ዛሬ የተለቀቁት።

በሰገን ህዝቦች ዞን ኮንሶ ወረዳ በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 251 ተጠርጣሪዎች 52 ተጠርጣሪዎች በሚቀጥለው ሳምንት የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ቢሮው አስታውቋል።

 

ክሳቸው የተቋረጡ ዜጎች ወደ ህብረተሰቡ ስቀላቀሉ የህግ የበላይነት በማክበር ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በመልካም ተግባር እንዲክሱ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።

በካሳዬ ወልዴ እና ጥበበስላሴ ጀምበሩ