የከተሞች የምግብ ዋስትና አካል የሆነው የልዩ ተጠቃሚዎች መርሀ ግብር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተሞች የምግብ ዋስትና አካል የሆነው የልዩ ተጠቃሚዎች መርሀ ግብር ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

ካለፈው አመት ጀምሮ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር በ10 አመት ውስጥ በ972 ከተሞች የሚገኙ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በመርሀ ግብሩም የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢ ልማት ተሰማርተው እየሰሩ እና በቀጥታ ድጋፍ ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር አካቶ እየተተገበረ ነው።

በዚህ መርሃ ግብር የተካተተውና የልዩ ተጠቃሚዎች ፕሮግራም ግን ልየታን ጨምሮ ሌሎች ጥናቶች መደረግ ስለነበረባቸው ባለፈው አመት ተግባራዊ መሆን አልቻለም ነበር።

በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ የሚሆኑትንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ በልመና የሚተዳደሩ ተጠቃሚዎችን፥ የመለየት፣ ካሉበት ህይዎት እንዴት ማውጣት እንደሚቻል፣ የሚደረጉላቸው ድጋፎችና መሰል ጉዳዮችን ለመለየት ጥናት ሲደረግ ቆይቷል።

ጥናቱ በየትኞቹ ከተሞች የሚገኙ ተጠቃሚዎች በፕሮግራሙ እንደሚካተቱ ለመለየት ያስችላልም ተብሏል።

አሁን ላይም ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ከፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተያዘው አመትም ልዩ ተጠቃሚዎቹ ወደ መርሀ ግብሩ እንዲገቡ እንደሚደረግ በኤጀንሲው ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።

ለመርሃ ግብሩ ከ74 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፥ ከ4 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በጥናቱም ተጠቃሚዎቹ አሁን ያሉበትን ህይዎት መቀየርና ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ምላሽ ይኖረዋልም ነው ያሉት።

ተጠቃሚዎቹ ከሚደረግላቸው ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ራሳቸውን ሊለውጡ የሚችሉባቸውን መፍትሄዎች ማከናወንና ማህበራዊና ስነልቦናዊ ስልጠናዎችን በመስጠት ክትትል እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ትምህርትና የጤና አገልግሎትን በነፃ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር እንደሚኖርም ተገልጿል።

መርሀ ግብሩ ከዚህ አመት ጀምሮ በየአመቱ በምግብ ዋስትናው ውስጥ ልዩ ተጠቃሚዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን