የጥምቀት በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችለው ሰነድ በመጪው መጋቢት ለዩኔስኮ ይቀርባል

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀትን በዓል በማይዳሰስ ወካይ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የማስመረጫ ሰነዱን በመጪው መጋቢት ለዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) እንደሚቀርብ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

በባለሥልጣኑ የባህል አንትሮፖሎጂስትና የማስመረጫ ሰነድ ዋና አዘጋጅ አቶ ገዛኸኝ ግርማ እንደገለጹት፥ አንድን ማህበራዊ ክዋኔ በማይዳሰስ ወካይ የዓለም ቅርስነት ለማስመዘገብ በዩኔስኮ መስፈርቶች መሰረት የማስመረጫ ሰነድ ተዘጋጅቶ መቅረብ አለበት።

በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች ለምዝገባ የሚያስፈልጉ አምስት መስፈርቶችን ያካተተ የማስመረጫ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው።

መስፈርቶቹ ቅርሱ በብሔራዊ ደረጃ መመዝገቡ፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ይሁንታ በፅሁፍና ቃለ መጠይቅ መረጋገጡ፣ የቅርሱ ምንነት እና አበርክቶ እንዲሁም ስለወደፊት ጥበቃው ሙሉ መረጃዎች መሰነዱ፣ ቅርሱን ሊወክል የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ዶክመንተሪ እንዲሁም የቅርስ መገለጫ አስር ምስሎች መምረጥ የሚሉ ናቸው።

እስካሁንም በተከናወኑ ተግባራት ቅርሱን በአገራዊ ቅርስነት የማስመዝገብ፣ የበዓሉን ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ፋይዳ የሚያስቃኙ መረጃዎች ስብሰባና የሕብረተሰቡን ይሁንታና ተሳትፎ በዋናነት ከጎንደር፣ ላልይበላ፣ አክሱምና አዲስ አበባ ክብረ በዓላት የማረጋገጥ ሥራዎች ተጠናቀዋል።

አጠቃላይ መረጃዎች ዝግጅት፣ የቅርሱ ወካይ የ10 ደቂቃ ዶክመንተሪና ለወካይነት ከተነሱ አንድ ሺህ ፎቶዎች መካከል አስሩን የመምረጥ ሂደትና ሌሎች ተግባራት በቅርብ ጊዜ እንደሚጠናቀቁም አቶ ገዛኸኝ አረጋግጠዋል።

ከዛሬ አመሻሽ ጀምሮ ነገ በሚከበረው በዓለ ጥምቀት አስፈላጊውን መረጃ ለመሰብሰብ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጎንደር የሚገኙ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ቀሪ ሥራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

የማስመረጫ ሰነዱ ለዩኔስኮ ከተላከ በኋላ በድርጅቱ ድረገጽ የሚለቀቅ ሲሆን፤ የማስመረጫ ሰነዱ ተገምግሞ በቅርስነት ምዝገባ ማለፍና አለማለፉ የሚለየው ከአንድ ዓመት ከ6 ወራት በኋላ ነው።

በዚህም ውሳኔው በሕዳር 2012 ይፋ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።

የማስመረጫ ሰነዱ በመጪው መጋቢት ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ተጠናቆ እንደሚቀርብ አቶ ገዛኸኝ ገልጸው፥ ሕብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ለሚደረገው አጠቃላይ ዝግጅት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንደ ጥምቀት ዓይነት ባህላዊ ሥነ-ሥርዓቶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ጎብኚዎችን እና ተመራማሪዎችን በመሳብ፣ ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅና የአገር ገጽታን በመገንባት ረገድ የሚኖራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ እንደሆነም ገልጸዋል።

ቅርሶችን ለማልማት፣ ጥበቃ ለማድረግና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግም ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የመስቀል፣ የሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫን የፍቼ ጨምበላላ እና የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓትን በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ የዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን፥ በዓለ ጥምቀት ከተመዘገበ ባለ አራት የማይዳሰሱ የዓለም ባሕላዊ ቅርሶች ባለቤት ያደርጋታል።

የሰሜን ተራሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው የሚታወቅ ነው።

ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፥ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር በ2003 በዩኔስኮ ጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀውን የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ስምምነት የፈረመችው በየካቲት 24 ቀን 2006 ነበር።