ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በተወሰኑ የፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀጾች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ተግባቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በሞራል ካሳ ፈንድ፣ በሽብርተኝነት ትርጓሜና በሌሎች የጸረ-ሽብር አዋጅ አንቀጾች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በመደራደር ላይ የሚገኙት ኢህአዴግና 14ቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች 'በጸረ-ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር አለባቸው' ተብለው በቀረቡ አንቀጾች ላይ ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ ድርድር አካሂደዋል።

"አዋጁ ከአገሪቷ ህገ-መንግስትና ከወንጀል ህግ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ህጎች ጋር ይጣረሳል” በሚል በተደራዳሪ ፓርቲዎች ባለፈው ወር ለቀረቡ ሃሳቦች ገዢው ፓርቲ ዛሬ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

በዚህም የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀፆች ከህገ-መንግስቱ አንቀፆችና ከወንጀል ህጉ ጋር ያላቸው ተያያዥነት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ህጎች፣ ስምምነቶችና ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች አንጻር ያለውን ተዛምዶ በዝርዝር ማብራሪያ አቅርቧል።

የፀረ ሽብር አዋጁ ከህገ-መንግስቱ ፣ ከአገራዊና ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች ጋር የተጣጣመና የማይቃረን መሆኑንም ለተደራዳሪ የተቀዋሚ ፓርቲዎች አስረድቷል።

በመሆኑም "አዋጁ ከአገሪቷ ህገ-መንግስትና የወንጀል ህግ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ህጎች ጋር ይጣረሳል” የሚለውን የተደራዳሪ ፓርቲዎች ትችት ለመቀበል "አሳማኝ ምክንያት አላገኘሁበትም" ሲል ገዢው ፓርቲ ምላሽ ሰጥቷል።

ተጣምረው የሚደራደሩት 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች የአዋጁ ስድስት አንቀጾች መሰረዝ፣ አምስት አንቀጾች ደግሞ መሻሻል አለባቸው በሚል ያቀረቡትን የድርድር ሃሳብ እንደማይቀበለውም ነው ገዢው ፓርቲ አቋሙን የገለጸው።

በተደራዳሪ ፓርቲዎች እንዲካተቱ የቀረቡ አዳዲስ አንቀፆችም በወንጀል መቅጫ ህጉ የተካተቱ መሆናቸውን በማስረዳት እንደ ማይቀበሉዋቸው የገዢው ፓርቲ ተደራዳሪዎች አስረድተዋል።

መሰረዝና መሻሻል አለባቸው የተባሉ የአዋጁ አንቀጾች ከአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት፣ የህዝቡን ሠላምና መረጋጋት ከመጠበቅና የህግ የበላይነት ከማስከበር አኳያ ጠቃሚ ናቸው በማለትም ምክንያቱን በዝርዝር አስቀምጠዋል።

በጸረ-ሽብር አዋጁ ከአንቀጽ 3-12 የተዘረዘሩት የቅጣት ደረጃዎች ከሌሎች አገሮች የፀረ ሽብር አዋጆች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን የገዢው ፓርቲ ተደራዳሪዎች አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ አሳማኝ ምክንያቶች ከቀረቡ ሊያሻሽላቸውና ሊያስተካክላቸው የሚችሉ መሆናቸውን ነው የተገለፀው።

ፓርቲዎቹ ባደረጉት ድርድር በአሸባሪነት ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ጉዳያቸው ተጣርቶ በነፃ ከተለቀቁ በኋላ የሞራል ካሳ የሚያገኙበት ፈንድ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ገዢው ፓርቲ "ሽብርተኛና ሽብርተኝነት" የሚለውን የአዋጁን ትርጓሜ ግልፅ ከማድረግ አኳያም የተሻለ ስያሜና ትርጉም ከቀረበ ለመቀበል መስማማቱን ገልፀዋል።

በጸረ-ሽብርም ይሁን በወንጀል ህጉ ላይ ፖሊስ ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅዱ አንቀፆች ተፈፃሚነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን ለመወሰን ደረጃውን የጠበቀ የህግ ማዕቀፍ እንደሚወጣም እንዲሁ።

በድርድሩ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ከድርድሩ ደንብ ውጪ በሚያሳየው የስነ-ምግባር ጥሰትና በሰጠው መግለጫ ከተደራዳሪ ፓርቲዎቹ ቅሬታዎች በመቅረባቸው የሚዲያ ኮሜቴው መርምሮ ሪፖርት እንዲያቀርብ ተወስኗል።

ፓርቲዎቹ በዛሬው ድርድራቸው በአዋጁ ላይ የሚካሄደው ድርድር የማጠቃለያ ውጤትና የፓርቲዎቹን የአቋም መግለጫ በቀጣይ ለመስጠት በመስማማት በቀጠሮ ተለያይተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ