የ7ኛው ህወሓት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የአቋም መገለጫ

እኛ ከ2 ሺህ በላይ የህወሓት ካድሬዎችና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከ200 በላይ የእህትና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ከጥር 3 ቀን እስከ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ላይ በመገኘት ጥልቅ ግምገማ በማካሄድ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ያለምንም ማመንታት የገመገመውንና የሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ የጎደለው ካለ ለመሙላትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ በተጨማሪም ከህዝብ፣ ድርጅት፣ ክልልና ሀገር አንፃር የፈጠርናቸው ችግሮች በልኩ በመውሰድ ከራሳችን ጋር ለማያያዝ ችለናል።

ትእግስተኛ እና ቻይ የሆነው ህዝባችን በድርጅቱ ላይ ፅኑ እምነት በመያዝ ከእምነቱና ልምዱ ተነስቶ ይህንን እድል ስለሰጠን የላቀ ምስጋና ሳናቀርብ አናልፍም።

እስካሁን ያስመዘገብናቸው ክልላዊና ሀገራዊ ስኬቶች ሀገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተመራች ያስመዘገበችው ደማቅ ክንውኖች መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው።

የክልላችን ህዝብ፣ በሀገርችንና አለም የመሰክርላቸው የሚያስጎመጁ ስኬቶች እያረጋገጥን ወደፊት እየተምዘገዘግን እንዳለን የሚታወቅ ነው፤ ይህንን ደግሞ አለም አቀፍ ተቋማት በተለያየ መንገድ ያረጋገጡት ሀቅ ነው።

ከእህትና ከአጋር ድርጅቶች ጋ በመተባበር በመርህ እና በመተሳሰር የተመሰረተ አንድነትን በማጠናከር የሀገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስታዊ ስርአታችን ስር በማበር የጀመርናቸው የተሃድሶና ትራንስፎርሜሽን የማረጋገጥ ጉዞን ለማሳካት ዛሬም እንደቀደሙ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምናሳካው አንጠራጠረም።

ይህ በንዲህ እንዳለ በአሁኑ ጊዜ አገራችን በጣም የሚያሳዝን አጣብቂኝ  ውስጥ የገባበችበትና በፈጠረነው ፖሊቲካዊ ችግር ህዝብና አገር ባስመዝገብናቸው ስኬቶች ልክ ሁሉን አቀፍ ችግር፣ ውድመት፣ ሞትና መፈናቀል እንዳስከተለ ህዝብ በድርጅቱና መንግስት ላይ የነበረው ተስፋ እና ማጣጣም የጀመረውን ልማትና ሰላም እንዲያጣ እንዲሁም መጪው እድሉ ጨልሞ እንዲታየው አድርገናል።

የሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች እንዲህ ያለ ክህደት፣ ህዝባዊነትና አብዮታዊ ስብእና የሸረሸረ ጉደለት፤ በጣም እንዳሳዘነን፣ በፈፀምናቸው ችግሮች ልክ ህዝብን በተግባር ልንክስ ቃል ኪዳናችን አድሰን እንገኛለን፡፡

ይህንን ሳናደርግ ብንቆይ ደግሞ ተመሳሳይ የመታደስ እድል እንደማናገኝ፣ በ1993 ዓ.ም ተሃድሷችን ነጥረን እንዳወጣነው አርማጌዶን መጠፋፋትና እልቂት አንደሚያስከትል ከልባችን አምነን ተቀብለናል፡፡

በዚህ መሰረት ከተደረገው ግምገማ በመነሳት በየደረጃው በግምገማና ግለሂስ በማጥለቅ በቀጣይነት የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ የጠበቀ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ በመግባባት ስብሰባውን ጨርሰናል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከ43 ዓመት በፊት ትግሉን ሲጀምር እንደሚታወቀው ትግሉ ረዥምና መራራ፤ ድሉም የግድ እንደሆነ አምኖ ሁሉን አቀፍ ትግልና መስዋእትነት በመክፈል ኃያልነቱን፣ ህዝባዊነቱን፣ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን በተግባር ያስመሰከረ ድርጅት ነው።

በትግሉ ጉዞም ባለበት መቆምና በእሽክርክሪት ዙርያ መንከራተት ሲያጋጥመውም ስትራቴጂካዊ አመራርና ራእይ እያስቀመጠ ውስጣዊ ድክመቱን በማያዳግም በመገምገም ከመድረክ ወደ መድረክ እየተሸጋገረ፤ መድረኩ የሚጠይቀውን ሁሉም አይነት መስዋእትነት እየከፈለ ለህዝብና ለታጋዩ ያለው ተቀባይነት ይበልጥ እየደመቀ፣ ሁሉንም አይነት ውድቀትና ኋላቀርነት በብልሀት እየተሻገረ ያለምንም ስስትና መጠራጠር መስዋእትነት እየከፈለ ምርጦችን ቀብሮ ፣ ምርጦች እየተካ የመጣ ድርጅት ነው፡፡

ምንም እንኳ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት በየደረጃው እየተረጋገጠ ቢመጣም፤ በየደረጃው የሚገኘው ስትራቴጂክ አመራር የድርሻውን ባለመጫወቱ ምክንያት መልሶ ወደ ጥገኛ መበስበስ፣ ጉደለት እና ብልሽት ሰምጠን፤ ህዝብ፣ ድርጅትና አገር በከባድ ቀውስና የመበታተን ጡዘትና እልቂት እንዲገባ አድርገናል።

በየደረጃው የሚገኝ ካድሬና አመራር ከህዝቡና ከመስመሩ አላማ በላይ ግለኝነት ተጠናውቶት፣ የበኩርና የመጨረሻ ልጁን ኣሟጦ የሰጠውን ህዝቡን ክፉኛ እንዳናደደውና እንደበደለው አምኖ ተቀብሏል።

በመጀመሪያው የ2009 ዓ.ም በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴያች ጠልቆና ወደ እያንዳንዱ ሰው ወርዶ ባለመሰራቱ የጥገኛ የመበስበስ አደጋ ጉድለት አገርሽቶበት፣ ኔትዎርክና መጠቃቃት ገኖ፡ ስልጣን እንደ መኖሪያ ተወስዶ አመራሩን አኮላሽቶና አስሮ ስለያዘው፤ ይባስ ብሎም በውሸት ሪፖርት ልቡን የሚነፋና የሚጎረን፣ በተወሰኑ ስኬቶች የሰከረ አመራር እንደተፈጠረ ኮንፈረሰኛው በዝርዝር ተወያይቶና ተከራክሮ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

ተልእኳችንና ፓለቲካዊ ስብእናችንን ረስተን፣ የጥገኛ መበስበስ ጉደለት ወደሚታይበት መድረክ የተሸጋገርን መሆናችንን በጥፋቱ ልክ አምነን ተቀብለነዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፀረ ዴሞክራሲ፣ ኔትዎርክ ያጥለቀለቀበት፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር እጦት የተጓደለበት፣ የአመራር መርህ ላይ የተመሰረተ አንድነት የተኮላሸበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ይህ ደግሞ በትግራይ ህዝብ እና በህወሓት መካከል የነበረውን በደም የተሳሰረና የፀና ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል።

በከፋ መልኩ ደግሞ በየደረጃው ያለው ካድሬና አመራር ወደ ስልጣን ሽኩቻና ሽምያ ገብቶ የገዥ መደብ ጠርዝ ተቆናጦ የሚሻግር አቅም አጠራቅሞ የቆየ መሆኑን ሰባተኛው የህወሓት ድርጅታዊ ኮንፈረንሰ ተሳታፊ የሆነው ካድሬና ከፍተኛ አመራር ያለምንም ማወላወል ገምግሞ አረጋገጧል፡፡

ስልጣንን እንደ መኖርያ በመውስድ ለጥገኛ መበስበስ እየተዳረገ መሆኑን በማመን የፈፀመውን ታሪካዊ ስህተት በማመን ህዝቡን ለመካስ ቃሉን የሚያድስበት መድረክ ሁኖ አግኝቶታል፡፡

ስትራቴጂካዊ ተልእኮውን ያመከነ አመራር ከዚህ በፊት የቆየ በተዳፈነ አገላለፅ ትራንስፎርሜሽን አልተሳካም በሚል የተለመደ ማባባያ እና ለውጥ የማያመጣ የግምገማ ስልት፣ መሬት ላይ የሌለ ሪፖርትና መረጃ በማየት፣ በተወሰኑ ሰኬቶች የሚሰክር በፈጠራቸው ጉድለቶችና ብልሽቶች ደግሞ ክልላችን ሀገራችን በከፋ ሁኔታ እንድትናወጥና እንድትታመስ የራሳችንን ድርሻ ነበረበት፡፡

በዋነኝነት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ባልበላበትና ባልተቀየረበት እንደጠገበና እንዳለፈለት የሚያስመሰል ቅጥፈት ካድሬውና ከፍተኛው አመራር እየመገበው እንደመጣ ውስጡን ፈትሾና ረግሞ እንዳይደገም እንዲታገል ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

ከ27 በመቶ በላይ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ፤ በዋነኝነት ደግሞ በሚልየን የሚቆጠር የትግራይ ህዝብ በሴፍቲኔት የሚተዳደር፣ በከተማም ጭምር ከድህነት ያልወጣ ህዝብ ተሸክሞ፣ በፍፁም የፀረ ህዝብና መስመር ቁርቁስ የገባ ካድሬና አመራር እንደነበር አጉልቶ ያሳየ መድረክ ሁኖ ኮንፈረንሳችን ተጠናቋል፡፡

የሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንሰ ተሳታፊ፤ በመርህ ላይ ባልተመሰረተው አንድነት ጠንካራውንና የጋራ የድርጅታችን እሴቶች እንደጎዳው ተሳታፊው ካድሬ አምኖ ተቀብሎታል፤ እነዚህ የድርጅታችን እሴቶች መሸርሸር ዋናው ምንጩ ራሱ ከፍተኛው ካድሬና አመራር መሆኑን ያላንዳች ማዋላወል ተቀብሎታል፡፡

በአገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታም አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ጎልብቶ እንዳይወጣ ድርሻ መጫወቱንና ይህንን ደግሞ የድርጅታችን አቅም አኮላሽቶታል፡፡ ስለሆነም ያልተገባና እጅግ አሳፋሪ ተግባራት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነናል፡፡ የመሪነትና የካድሬ ያበረ ውስጣዊ የድርጅታችን አቅም ተዳክሞ፣ የህዝብ ችግር በተቀላጠፈ አኳኃን መፍታት ያልቻልንበት፤ በእርካታና የተሳሳተ መረጃ እውነተኛ የህዝባችን ተጠቃሚነት በመጉዳት ረገድ ካድሬውን የላቀ ድርሻ መጫወቱን በዝርዝር ተገምግሞ መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡

ባለንበት ሁኔታ ሰላም አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፤ አገርና ህዝብ ለማዳን ብቻ ሳይሆን ራሳችንም ለመዳን ካልሰራን ሁኔታዎች እየከፉና እየተባባሱ በሁከትና ብጥብጥ እንምንጎዳ፤ የከፋ ጉዳትና መከራ እኛ ላይ እንደሚብስ ግልፅ መሆኑ የሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በተሳታፊዎች በሙሉ እምነት ተቀብሎታል፡፡

ይህንን አገር የማዳን ጥያቄ፤ የህዝብና የህወሓት አጀንዳ ብቻ አለመሆኑ በማመን ከእህት ድርጅቶቻችን ጋር በትግል የተመስረተ አንድነት በመፈጠር እስከ አሁን ድረስ የበደልነውና ያጠፋነው ለመካስና ተጨባጭ ለውጥ ለማጣት ለነገ የማይባል ጉዳይ ሆኗል፡፡

የየራሳችን የቤት ስራ በመፈፀምና ቆሻሻችንን በማስወገድ ወደፊት እንጓዛለ፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንደ ድርጅት ወደፊት፤ ሌላው ወደ ኋላ ለመጓዘ ከሞከረ፤ ተያይዘን ገደል እንደምንገባ አውቀን ከመናቆርና ከመወነጃጀል በመወጣት ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሙሉ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ በመነሳት ያስመዝገብናቸው ክልላዊና ሀገራዊ ስኬቶች፣ ሀገራችን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተመራች ያስመዘገበችው ደማቅ ክንውኖች ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ጠንከረን መስራት ይገባል፡፡ የክልላችን ህዝብ፣ ሀገራችንና አለም የመስከረላቸውና የጎመጁለት ስኬቶች ወደ ማይቀለበሱበት ደረጃ እንድናደርሳቸው አደራችንን ማጠናከር ይገባል፡፡

የጀመረነው የሚያስጎመጅ ልማትና እድገት አሁንም የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርገን ለማሳካት መረባረብ ይገባናል፡፡

ክቡራትና ክቡራን

የሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንሳችን ግምገማ ከተለመደው በአይነቱና ይዘቱ የተለየ ሆኗል፡፡ በውጤቱም የትግራይ ህዝብ በድርጅቱ ህወሓት ገና ተስፋ ሳይቆርጥ እንዲያውም ድርጅታችን እንደ ልማዱ እንዲስተካከልና እንዲነቃቃ ያነሳው የነበረው ፍላጎት አለምልሞታል፡፡

ለዚህ ታጋሽ፣ ታታሪና አርቆ አሳቢ ህዝባችን በድጋሜ ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረብን ፤ ይቅርታም እየጠየቅን ቃላችን ሳናጥፍ እንደምንክስ እያረጋገጥን ከዚህ በታች ያለውን ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1. እኛ የህወሓት ከፍተኛ አመራርና ካድሬዎች በድርጅታችን ተከስቶ ያለውን የጥገኝነት መበስበስ አደጋና ወደ ገዥ መደብ የመለወጥ አዝማሚያ፤ ለዚሁ እንደ ማዳበሪያ የሚያገልግሉ ቡድተኝነት፣ ኔትዎርክ፣ መጠቃቃትና መከላከል፤ የስልጣን ሽኩቻና የግል ክብርን ከመስመርና ከህዝብ በላይ የማድረግ አለማ ያነገቡ የፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ህዝብ ተግባራት መሆናቸው በመረዳት፤ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆች በመነሳት ለህዝባችንና መስመራችን ቅድሚያ እየሰጠንና መሳሪያችን በማድረግ በጥንካሬ እየታገልን የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መሰመራችን የሚጎለብትበትና ህዝባችን ከዚህም በላቀ ተጠቃሚ እንዲሆን በወኔና በላቀ ቁጭት እንደምንታገል ቃል እንገባለን።

2. እኛ የህወሓት ከፍተኛ አመራርና ካድሬዎች፤ ህዝባዊና ውግንና ባህርያችንን የሚሸረሽሩ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ የትግል አንድነት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ጉደለቶች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደማሪ አቅም እየፈጠርን የህዝባችን ጥያቄ መልስ እንዳሰጥ የሚከለክሉን፣ ለስልጣን ካለን የተዛባ አመለካከት የሚነሳ መጠቃቃት፣ ቡድንተኝነት፣ ኔትዎርክና አላስፈላጊ ቁርኝቶችና ችግሮች ፤ በሰፊው ሁሉን አቀፍ የህዝባችንን ተሳትፎ በማጀብ ችግሮቻችንን በሚፈታ አገባብ ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለ ትግል እንደምንለኩስ ቃል እንገባለን፡፡

3. በጽኑ መሰረት ያለውን የህወሓት መስመር ተጠቅመን ለእንደዚህ አይነቱ ብልሽትና እኽክርክሪት እድልና ጊዜ የሌለን መሆናችን ተረድተን የድርጅታችን ለማመን የሚያስቸግሩ የትግል ታሪክ ጠብቀን፤ የግል ጉዳይ፣ ከመስመርና ከህዝብ በታች አድረገን፣ የሚስተካከለውን አስተካክለን አቅማችን በማደራጀትና ተጠናክረን እንድንሰራ እና ለልባሙ አስተዋይና ታጋይ ህዝባችን እንደምንክስ ቃል እንገባለን፡፡

4. ባለፉት ጊዜዎች አጋጥሞን በነበረው ችግር ምክንያት ያባከነው የልማት ኃይል፣ ግዜና ሌሎች እሴቶች እንዳሉ በይፋ ተረድተናል፤ እኛ የህወሓት ካድሬዎችና ከፍተኛ አመራሮች ታገሎና እንድገታል አድርጎ ለዚሁ ደረጃ ላበቃን የትግራይ ህዝብ፣ ለነባር አመራር፣ ታጋዮች፣ የጦር አካል ጉዳተኞች እና የሰማእታት ቤተሰብ የሚገባቸው ክብር ሳንሰጥ፤ በትናንሽ ስኬቶች ሰከርን፣ በውሸት ሪፖርት እየተሞጋገስን፣ ያልበላ ህዝብ እንደበላ እያስመሰልን፣ በመቆየታችን ምክንያት መስራት ያለብን ስራዎች ባለማከናወናችን 27 በመቶ የትግራይ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዲኖር ምክንያት ሆነን ቆይተናል፤ በመሆኑም ይህ ከባድ ክህደት በፍጥነት እንዲታረም ህዝቡ ከድህነት መላቀቅ ስለሚገባው ህዝባችን ለመካስ ጠንክረን የምንሰራ መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡

5. ድርጅታችን ህወሓትና ህዝባችን በልማትና ትራንስፎርሜሽን ሂደት ባደረጉት ጥረት በተለይም በግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች በክልላችን ያስመዘገብነው ደማቅና እውቅና ያገኘ ስኬት መኖሩን የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያጋጠመን የጥገኛ መበስበስ አደጋ ለእድገትና ትራስፎርመሽን ድሎች የሚያደናቀፍበትና ፍጥነቱ የሚገታበት፣ የማኑፋክቸሪንግ ትራንስፎረሜሽን ጉዞ፣ ትርጉም ያለው ስራዎች ያልተከናወነበት እንዲሁም በትምህርት ጥራትና የጤና አገልግሎት አበይት ጉድለቶች የታዩ መሆናቸው የህወሓት ማአከላዊ ኮሚቴ ስትራተጂካዊ አመራር የገመገማቸው ፈተናዎች፤ በኮንፈረንሱ መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡ ስለሆነም እኛ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎች፣ ጉደለቶቹን በአስቸኳይ ለማስተካከል በሙሉ እምነትና ዝግጁነት ህዝባችንን በተግባር ለመካስ ቃል እንገባለን፡፡

6. እኛ የድርጅታችን ህወሓት ካድሬዎችና ከፍተኛ አመራር የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከሞላጎደል ለመፈፀም የሚያደናቅፍ አመላካከትና ተግባር በመታገል፤ በዋነኝነት የልማቱ አቅም እንድትሆኑ ብቁ የአመራርነት አቅም እንደምናሳርፍ እየገለፅን እናንተም አንደወትሮ ጥረታችሁን በማጠናከር ከድርጅታችሁ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

7. የምሁራኖቻችንን አቅም አሟጠን እንድንጠቀም እና ሁሉም ስራዎቻችን በጥናትና ምርምር መመስረት እንዳለበት፤ ምሁሩ ከመጀመርያ እቅዶቻችን ጀምሮ እንዲሳተፍ፣ አስተያየት እንዲያስቀምጥና እንዲተገብረው፣ ለህዳሴያችን ለውጥ መሪ ሁኖ ማሳካት የሚያስችል አሰራር እያሰፋን ጥልቀት ባለው መልኩ እንድንጓዝ፣ ይህንን የሚያደናቅፍ አመለካከትና ተግባር ያለማወላወል ለማረም ቃል እንገባለን፡፡

8. አመራራችን ዋናው ጉዳይ የሆነው አላማና ህዝብን መሆኑን ቀርቶ ህዝባዊነቱ ተሸረሸሮ፤ ስልጣንን እየተሻማ ህዝብና አገርን አደጋ ላይ ወድቆ፤ ህዝብ በስጋትና በምሬት እየኖረ እንደ መንግስትና ድርጅት፤ህዝብ የማዳመጥና ተገቢ ምላሽ የመስጠት አቅሙ እየተዳከመ፣ የህግ የበላይነትና ፍትህ በሙሉ አቅም ከማረጋገጥ ፋንታ አልፎ አልፎ የፍትህን መዋቅር የመጠቃቂያ መሳርያ ሁኖ የሚታይበት ሁኔታ መፈጠሩን በጥልቀት በመረዳት መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ጉዳይ በጊዜ የለንም መንፈስ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቃል እንገባለን፡፡

9. በትግራዋይነትና በድርጅታን ስም የሚነግዱ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ የትምክትና ጠባብ ኃይሎች፤ በድርጅታችን፣ ህዝባችን፣ ክልላችንና አገራችን እየደረሰ ያለው አሉታዊ ጫና ሆነ ተብሎ በተፈጠረና በመሬት ላይ የሌለ ህገ መንግስታዊ ስርአታችን የማይፈቅደው ሁኖ ሳለ፤ የትግራይ ህዝብና ህወሓት የበላይነት አለ በሚል ሆን ተብሎ በተቀረፀ አጀንዳ ፌዴራላዊ ስርአታችን ለመበተን ታቅዶ የተጠነሰሰ ሴራና ተንኮል መሆኑን ተረድተን በጽናትና በጥንካሬ እንደምንታገለው ቃል እንገባለን፡፡

10. ድርጅታችን ይዞትና ጀምሮት ያለውን የትውልድ መተካካት ሂደት፤ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥልበትና ወደ ኋላ የማይመለስበት ሁኔታ እንድምንፈጥር እያረጋገጥን፤ እያንዳንዱ ትውልድም ከአያቶቹ የበለፀገ ታሪክና ተሞክሮ በመማር ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ፤ እንከን የማይወጣለትን የህዝባዊነትና ሩቅ አሳቢነትን ተጠቅሞ እያንዳንዱ መድረክ የሚጠየቀው እውቀትና ክህሎት ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝባዊ አስተሳሰብ አቅም እንዲኖረውና እንዲላበሳቸው በማድረግ በተግባር የተፈተኑ የመፃኢ ምርጥ መሪዎች እንዲፈጠሩ ጠንክረን እንሰራለን፡፡

11. አመራራችን የግል ጥቅሙን በማስቀደሙ ምክንያት በኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር መኖሩን የድርጅታችን ስትራተጂካዊ አመራርም ሆነ እኛ ከፍተኛ አመራር ገምግመናል፤ ሆኖም የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ በተገቢው አገባብ መታየት እንዳለበትና ቀጣይ ትግሎች እንደሚያስፈልገው፤ ችግር ያለበት አመራር ካለም ተጠያቂ ለማድረግ ጠንክረን እንደምንታገል ቃል እንገባለን፡፡

12. የሙያ ማህበራት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣ ሚድያዎች ነጻነታቸውን በማረጋገጥ ራሳቸውን ችለው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ነጻ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ድርሻቸውን እንዲወጡ በተጨማሪም የቆሙለትን አለማ እንዲያሳኩ ከፍተኛ ድጋፍ እንደምናደርግ እያረጋገጥን የአደረጃጀቶቹና የተቋማቱ አቅም የሚያዳክም ማንኛውም ጣልቃገብነት በፅናት እንደምንታገል ቃል እንገባለን፡፡


የተከበራችሁ እህትና አጋር ድርጅቶች

ድርጅታችን ህወሓት አጋጥሞት የቆየውን ችግር የኛም ችግር ነው ብላችሁ ከልብ በማመን ባለፉት ሰባት ቀናት ከኛ ጋር ሆናችሁ ከጎናችን ሳትለዩ የግምገማችን አካል በመሆን ለሰጣችሁን ነጻነት የተሞላበት ገንቢ አስተያየትና ሀሳቦች ከልብ እያመሰግንን፤ በጥገኛ ኃይል ላይ የሚደረግ ትግል፣ በትግራይ ህዝብና በህወሓት የሚነግድ፣ በሌሎች ድርጅቶች ከመርህ ባፈነገጠ መልኩ ጣልቃ የሚገባ፤ የትም ይገኝ የትም እንደምንታገለውና እንደማንቋቋመው እየገለጽን በየአከባቢያችሁ ያለውን ጥገኛ ኋይል፤ ብሄርና ሃይማኖትን በማይለይ፣ ልማታዊ ባለሀብት በማይጎዳ መልኩ እንድትታገሉ ጥሪያችን እናቀርባለን።