የተሻሻለ የህጻናት ቲቢ መድሃኒት እየተሰራጨ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተሻሻለ የህጻናት ቲቢ መድሃኒት እየተሰራጨ መሆኑን የኢትዮጰያ መድሃኒት ፈነድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታውቋል።

የተሻሻለው መድሃኒት ለህጻናት ቲቢ ታማሚዎች ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙት ከነበረው መድሃኒት የአጠቃቀም ምቹነት እና እድሜያቸውን ከግምት ያስገባ የተመጣጠነ ይዘት ያለው መሆኑን ኤጀንሲዉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል።

የተሻሻለው የህጻናት መድሃኒት 75 በመቶ ራፋምፕሲን፣ 50 በመቶ አይናይዝድ፣ 75 በመቶ ራፋምፕሲን እና አይፎናይዝድን ከ150 በመቶ ታይራቪናማይድ ውህድን በመቀመር የተዘጋጀ ነው።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ፥ የተሻሻለዉ መድሃኒት በተለይ ለህጻናት ቀላል እና ለአወሳሰድም ምቹ አንዲሆን ተደርጎ የተቀመመ መሆኑን ተናግረዋል።

መድሃኒቱ ሙሉ በሙሉ ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የ27 ሚሊየን ብር ድጋፍ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው።

አሁን ላይ ከ20 ሺህ በላይ የ ቲቢ ህሙማን ህጻናትን የሚያገለግል የ14 ወራት የዚህ መድሃኒት ክምችት እንዳለ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

መድሃኒቱ በህክምና ተቋማት በነጻ በመሰራጨት ላይ ሲሆን፥ ከዚሁ ጎን ለጎነም የህክምና ባለሙያዎች ስለ ተሻሻለዉ መድሀኒት አጠቃቀም ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል ሰልጠና እየተሰጠም ነዉ ተብሏል።

 

በሀይለሚካኤል አበበ