ሀገራዊ የመስኖ ልማት ስርዓት ፍኖተካርታ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገራዊ የመስኖ ልማት ስርዓት ፍኖተካርታ ላይ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት ተካሄደ።

ውይይቱ የተካሄደው በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልና በአዲስአበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተዘጋጅቶ በቀረበው ረቂቅ ሀገራዊ የመስኖ ልማት ስርዓት ፍኖተ ካርታ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይም የአፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

pm_off.jpg

ሀገራዊ የመስኖ ልማት ሁኔታ እና የክፍተት ትንታኔ እንደሁም ተግዳሮቶች እና የአፈፃፀም አቅጣጫዎች አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ኢንጂኒየር መብሩክ መሐመድ ዝርዝር ማብራሪያዎች አቅርበዋል።

ፍኖተ ካርታው ሀገሪቱ እስካሁን በመስኖ ልማት የምትገኝበትን ደረጃና ዘርፉን ለማሳደግ በቀጣይነት መከናወን ያለባቸውን ተግባራት የሚያመላክት መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

እንዲሁም ወንዞችን በተለይም ሀገር አቋራጭ ወንዞችን በአግባቡ መጠቀም በሚቻልበት ዙሪያ ፍኖተ ካርታው መዘጋጀቱም ተነግሯል።

በተጨማሪም ፍኖተ ካርታው የተዘጋጀው በግብርናው ዘርፍ ዘመናዊነት ስለሚያስፈልግ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ በመስኖ ልማት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት ለልማቱ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው ከፍተኛውን በጀት እንደሚመድቡ ነው የገለጹት።

አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው ከ22-30 በመቶ ለመስኖ ልማት እንደሚያውሉ በመጥቀስ።

ኢትዮጵያ እስካሁን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ (ጂዲፒ) ለመስኖ ልማት የምትመድበው በጀት አነስተኛ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍኖተ ካርታው ይህን ጥያቄ በአግባቡ ሊመልስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

መንግስት የመስኖ ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ በማምረት ስራ የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በቂ የምርመር ስራ መስራት እንዳለባቸውና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱሰትሪ ትስስሩም በተጠናከረ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፍኖተ ካርታው ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ማገልገልና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ሁለት የትግበራ ዓመታትም ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ተሳታፊዎችም ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ሀገራዊ የመስኖ ልማት ስርዓት ፍኖተ ካርታ ላይ ጥያቄና አስተየት ያቀረቡ ሲሆን፥ በአቅራቢዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ተጠጥቶበታል። 

መድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በሰጡት የውይይት ማጠቃለያ መጠናቀቁን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ተጨማሪ መረጃ፦ ከኢዜአ