ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾመ፡፡

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ፣ ዶክተር ጀይሉ ዑመር እና ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የመጨረሻዎቹ እጩ ፕሬዚዳንቶች ተደርገው ለሚኒስቴሩ መላካቸው ይታወሳል።

ሚኒስቴሩም የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አድርጎ መድቧል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቦርድ በ2010 ዓ.ም ጥቅምት መጨረሻ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ እንዲቻል ከቦርድ፣ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች እና

ከኢንዱስትሪው የተውጣጣ የምልመላ እና ምርጫ ኮሚቴ በማዋቀር ስራ እንዲጀመር አድርጓል፡፡

ኮሚቴውም መመሪያውን መሰረት ያደረጉ እቅድና ዝርዝር መስፈርቶችን አዘጋጅቶ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትነት መወዳደር የሚፈልጉ አመልካቾችን ለመጋበዝ ማስታወቂያ በጋዜጣ አውጥቶ ነበር፡፡

በዛሬው እለትም የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አድርጎ መድቧል፡፡