በሀረሪ ክልል ሀማሬሳ አካባቢ በተከሰተ ሁከት የሰው ህይወት መጥፋቱን ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል ሀማሬሳ አካባቢ በተከሰተ ሁከት የሰው ህይወት መጥፋቱን የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ ሀማሬሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደራጁ የፀረ ሰላም ሀይሎች በተፈጠረ ሁከት የ4 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ነው ፖሊስ የገለፀው።

እንዲሁም በ10 ሰዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱ የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስረዲን አሊ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተደራጁና ሌላ ተልዕኮ ባላቸው ሀይሎች በተፈጠረ ሁከትም እህል ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰባት ከባድ ተሽከርካሪዎች ሙሉ ለበሙሉ መቃጠላቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ግምቱ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ ማሽኖች መቃጠላቸውንም ኮሚሽነር ነስረዲን አክለው ገልፀዋል፡፡

የሁከት ምክንያቱም በመጣራት ላይ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ በአሁኑ ሰዓት አካባቢው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል ብለዋል።

በሁከቱም ምክንያት በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ሞት ማዘናቸውንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቅም መጠየቃቸውን ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።