የደቡብ አፍሪካው ኤ.ኤን.ሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣን እንዲነሱ መወሰኑ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ ኤ.ኤን.ሲ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣን እንዲነሱ መወሰኑ ተነግሯል።

ፓርቲው ከውሳኔው ላይ የደረሰው ፕሬዚዳንት ዙማ በፍቃደኝነት ስልጣን እንዲያስረክቡ የቀረበለቻውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘገባዎች እያመላከቱ ነው።

የ75 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ዙማ ስልጣን እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልቀበልም ብለው ከቆዩ ለሀገሪቱ ፓርላማ ቀርበው የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥባቸው ይደረጋል ተብሏል።

ሆኖም ግን ፕሬዚዳንት ዙማ ከፓርላማው በቂ የመተማመኛ ድምፅ ማግኘት አንደማይችሉ ከወዲሁ ተገምቷል።

የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ ኤ.ኤን.ሲ በፕሬዚዳንቱ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ እና እቅዱን እስካሁን ይፋ አላደረገም።

ሆኖም ግን ፓርቲው ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ መወሰኑን የውስጥ ምንጮች አረጋግጠዋል ሲሉ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን እና ሬውተርስ ዘግበዋል።

ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ ደቡብ አፍሪካን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ተደጋጋሚ የሙስና ውንጀላዎች የሚቀርብባቸው ፕሬዚዳንት ዙማ ባለፈው የፈረንጆቹ ታህሳስ ወር ላይ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ /ኤ ኤን ሲ/ መሪነታቸውን ለክሪል ራማፎሳ ማስረከባቸው ይታወሳል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ