የኪነ ጥበበ የመከላከያ ሰራዊት ገፅታ ግንባታ ላይ የጎላ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኪነ ጥበበ ዘርፍ በመከላከያ ሰራዊት ገጽታ ግንባታ ላይ የጎላ አስተዋጾ ሊያበረክት ይገባል ተባለ።

6ኛው የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዎት ቀንን አስመልክቶ በኪነ ጥበበ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱም የኪነ ጥበበ ዘርፍ የመከላከያ ሰራዊት ሞራልን በመገንባትና በማነሳሳት ህብረተሰቡ ስለመከላከያ ሰራዊት አጠቃላይ ባህሪ እንዲገነዘብ የሚያስችሉ ስራዎች እየቀነሱ መመጣታቸው ተነስቷል።

ቀደም ባሉ ግዜያት የመከላከያ ሰራዊትን ለማነሳሳት እና ለማበረታታት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች በታላላቅ የዘርፉ ሰዎች ይሰሩ እንደነበር በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

አሁን ላይ ግን በኪነ ጥበበ ዘርፍ የመከላከያ ሰራዊት ሞራልን በመገንባትና በማነሳሳት የሚሰሩ ስራዎች መቀነሳቸውም በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

ለዚህ ችግር ናቸው ከተባሉት ውስጥም የባለሙያ እጥረት አንዱ ነው የተባለ ሲሆን፥ ለዚህ ደግሞ ለመከላከያ ማርሽ ቡድን አባላት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተገቢ ክፍያ አለመክፈል በምክንያትነት ተነስቷል።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን የመከላከያ ሰራዊት ሞራልን ለመገንባትና ለማነሳሳት ለሚሰሩ ስራዎች ተገቢ ሽፋን አለመስጠት እና የሚሰሩ ስራዎች የሚቀመጡበት ማእከል አለመኖርም በችግርነት ተነስቷል።

በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተካፈሉበት መድረክ ላይ በቀጣይ በዘርፉ ሊሰሩ ይገባል በተባሉ ስራዎች ላይ የሚደረገው ውይይጥ ቀጥሏል።

በትእግስት ስለሺ