መንገድና የንግድ ተቋማትን መዝጋት ከዛሬ ጀምሮ መቆም አለበት- ዶ/ር አብይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንገድና የንግድ ተቋማትን መዝጋት ከዛሬ ጀምሮ እንዲቆም የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር አብይ በመግለጫቸው፥ ህዝብ አንድ ላይ በመደራጀት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የራሱን መንግስት ማስገደድ እና ጫና በመፍጠር የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ወሳኙ ነገር ነው ብለዋል።

ሆኖም ግን ማንኛውንም ጥያቄ በምን መልኩ መቅረብ እንዳለበት እንዲሁም ግራ እና ቀኙን አስተውሎ መመልከት እና ማሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ይህም ህዝብ እና የሀገርን ሀብት በማይጎዳ መልኩ መሆን ይገባዋል ብለዋል ዶክተር አብይ።

በአሁኑ ወቅት ከስራ ማቆም ጋር ተያይዞ እየተነሱ ካሉ ጥያቄዎች ውስጥ “የታሰሩ ሰዎች ይፈቱልን” የሚል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑንም ዶክተር አብይ አስታውሰዋል።

ይህን ጉዳይ አመራሩ ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ ዋና ስራው አድርጎ በመውሰድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ተለቀው በተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ መወሰኑንም ነው የተናገሩት።

“እስር ከበዛ ህዝብ ይቸገራል፤ ማደግም ሆነ መለወጥ አይችልም” ያሉት ዶክተር አብይ፥ “ስለዚህ የእስረኞች መለቀቅ ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳችን በማድረግ እየሰራን ቆይተናል” ነው ያሉት።

አጀንዳ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ስራዎች መስራት እንደተቻለ አስታውሰው፥ ከጥልቅ ተሃድሶው ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ስልጣን ስር የነበሩን ከ30 ሺህ በላይ ሰዎችን ከእስር መፍታት መቻሉንም አስረድተዋል።

የፌደራል መንግስት መስራት ባለበት ጉዳይ ላይም ድርጅታቸው ጠንካራ ትግል ማካሄዱን ጠቅሰው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ጉዳያቸው በፌደራል ደረጃ እየታየ ካሉ ሰዎች ውስጥም ከግማሽ በላዩ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን አንስተዋል።

አሁን ላይ ድርጅቱ ህዝቡን የሚጠቅሙ ታላላቅ እርምጃዎችን መውሰድ በጀመረበት ወቅት የስራ ማቆም አድማን በማሳበብ በኦሮሞ ስም የግለሰቦች እና የመንግስትን ሀብት የመዝረፍና ማውደም ተግባራት እየተፈጸመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በክልሉ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችን ላይ ጥቃት መፈጸም፣ የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት የማድረስ እና መሰል ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ይህ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ያሉት ዶክተር አብይ፥ ይህንን እንቅስቃሴ ከለላ በማድረግ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላት እንዳሉና ጉዳዩ በህግ የበላይነት መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ህጋዊ መሆነ መንገድ ሰርቶ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት እንዳለውም ነው የገለጹት ዶክተር አብይ፥ አሁን እየተነሱ ባሉ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግስት ትኩረት በመስጠት እየሰራ ነው፤ ውሳኔ ላይም ተደርሷል” ብለዋል።

ስለዚህ ወጣቶች ሁሉንም ነገር በትእግስት መጠባበቅ እንዳለባቸውና መንገድ መዝጋት እና ሰዎች የንግድ ተቋማቸውን እንዲዘጉ ማስገደድ ትክክል አይደለምም ነው ያሉት ዶክተር አብይ።

አሁን አየተካሄደ ያለው ተግባር በአስቸኳይ መቆም እንዳለበትም ዶክተር አብይ አሳስበዋል።

አሁን እየተካሄደ ያለው ተግባር ወዳልተፈለገ አላማ ሊለወጥና የኦሮሞ ህዝብ እና ወጣቶችን ሊጎዳ ስለሚችል፥ የክልሉ ህዝብ እና ወጣቶች ከዛሬ ጀምረው ከስራ ማቆም ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ፦ ኦ.ቢ.ኤን