የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት 686 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ በጀት ለኮንግረሱ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ያለው ወታደራዊ በጀት እንዲጸድቅለት ለኮንግረሱ አቀረበ።

ፔንታጎን የ2019 በጀት አመት አጠቃላይ ወታደራዊ በጀትና እቅድ የያዘውን ወታደራዊ ሰነድ ለሃገሪቱ ኮንግረስ አቅርቧል።

በዚህም ለ2019 በጀት አመት 686 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ በጀት እንዲጸድቅለት ነው ጥያቄውን ያቀረበው።

ወታደራዊ በጀቱ ከ2017 አንጻር የ80 ቢሊየን ዶላር ጭማሪ አለው ተብሏል።

ከወታደራዊ በጀቱ ባለፈም የሃገሪቱን የሃይል ኤጀንሲ ጨምሮ ለሌሎች ተቋማት የሚሆን 30 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ በጀትም ጠይቋል።

የበጀት ጭማሪው አሜሪካ ከሩሲያና ቻይና እየገጠማት ያለውን ወታደራዊ ፉክክርና ስጋት ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል።

ዋሽንግተን አሁን ላይ ያጋጠማት ከባድ ወታደራዊ ፉክክር የደህንነቷ ስጋት እየሆነ መምጣቱም በሰነዱ ተጠቅሷል።

ይህን ለመቅረፍና ከሩሲያና ቻይና የተደቀነባትን ስጋት ለማስወገድም የሃገሪቱ ኮንግረስ ከፍተኛ የተባለውን በጀት ያጸድቀው ዘንድ ፔንታጎን ጠይቋል።

ሰነዱ አሁን ላይ ሩሲያና ቻይና ሌላውን አለም በራሳቸው እሳቤና አካሄድ ለመምራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ይጠቅሳል፤ አካሄዱ ለዋሽንግተን ስጋት መሆኑን በማንሳት።

ከዚህ ባለፈም ቻይና በደቡባዊ የቻይና ባህር በመስፋፋት በአካባቢው ያላትን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ወታደራዊ የበላይነት ከፍ ለማደረግ እየጣረች ስለመሆኗም አንስቷል።

ቤጂንግም በበርካታ አካባቢዎች የበላይ ለመሆንና ተፅዕኖዋን ለማጉላት የአጭር ጊዜ አቅድ አላትም ነው ያለው ሰነዱ።

በረጅም ጊዜ እቅዷ ደግሞ በወታደራዊም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መስኩ አሜሪካ አለም ላይ ያላትን የበላይነትም ሆነ ተሰሚነት የመቆጣጠር እቅድ እንዳላትም በሰነዱ ተጠቅሷል።

ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩና አማካሪው ዴቪድ ኖርኩይስት፥ ወታደራዊ በጀቱ አሜሪካ ከቻይናና ሩሲያ ሊገጥማት የሚችለውን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የቀረበው የአሁኑ ወታደራዊ በጀት አሜሪካ በተለያዩ ሃገራት የምታደርገውን ድጋፍ መቀነስና ማቋረጥንም ያካተተ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ በጀቱን ባስተዋወቁበት ወቅት የሃገራቸው ወታደራዊ በጀት፥ አለም ላይ ጠንካራው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ማቲስ ደግሞ ባለፈው ወር አሜሪካ በቻይናና ሩሲያ ላይ ያላት ወታደራዊ የበላይነት እቀነሰና እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልጸው ነበር።

 

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን እና ፕረስ ቲቪ