ፕሬዚዳንት ዙማ “በስልጣን ልቀቁ” ጥያቄ ላይ ዛሬ ምላሽ ይሰጣሉ- ፓርቲያቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ /ኤ ኤን ሲ/ ስልጣን እንዲለቁ ባቀረበው ይፋዊ ጥያቄ ላይ ዛሬ ምላሽ የሰጣሉ።

የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቼ ማጋሹሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ኤ ኤን ሲ ፕሬዚዳንት ዙማ ቶሎ ስልጣን እንዲለቁ ይፈልጋል ብለዋል።

ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ለመልቀቅ ከሶስት እስከ ስድስት ወር ጊዜ እንደሚፈልጉ ነው ዋና ፀሃፊው የተናገሩት።

በዙማ ስልጣን መልቀቅ ላይም ፓርቲያቸው ቀነ ገደብ አለማስቀመጡንም አመልክተዋል።

ኤ ኤን ሲ ዙማ የስልጣን ልቀቁ ጥያቄውን የማይቀበሉ ከሆነ በሀገሪቱ ፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ ወደ ማሰጠቱ እንደሚሄድ ተናግሮ ነበር።

ሆኖም ዋና ፀሃፊው የመተማመኛ ድምፅ በማሰጠቱ ላይ አሁን ላይ እርግጥ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ፕሬዚዳንት ዙማ ስልጣን ሲለቁም አሁን ላይ ምክትላቸው የሆኑት እና የኤ ኤን ሲ ሊቀመንበር የሆኑት ሲሪል ራማፎሳ እንደሚተኩም ዋና ፀሃፊው ተናግረዋል።

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ