በመዲናዋ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃ ፕሮጀክቶች ወደ ስርጭት አልገቡም

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የመዲናዋን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብለው የተቆፈሩ የምስራቅና የሰሜን አዲስ አበባ ሁለት ፕሮጀክቶች ወደ ስርጭት ሳይገቡ ለሁለት አመታት ቆመዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሳካት ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ስራ ቢገባም፥ አሁንም በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎች የውሃ እጥረቱ አልተፈታም።

በከተማዋ የሚስተዋለውን የውሃ እጥረት ለመፍታትም ሁለት ሰፋፊ የውሃ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደ አማራጭ መፍትሄ አድርጎ መውሰዱን ገልጿል።

በዚህ መሰረት በቀዳሚነት ከአንድ አመት በፊት የከተማዋን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባሉ ሁለት የውሃ ፕሮጀክቶች ቁፋሮ ስራ ተከናውኗል።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ ምስራቅና ሰሜን ክፍል የተከናወነ ሲሆን፥ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል።

የውሃ ፕሮጀክቶቹ ቢጠናቀቁም ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፕሮጀክቶቹ ወደ ስርጭት እንዳይገቡ እንዳደረጋቸው የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ሃይለማርያም ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የውሃ ፕሮጀክቶቹ ፈጥነው ወደ ስርጭት ካልገቡ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ሰለባ ትሆናለች።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በበኩሉ እንደ ችግር የተነሳው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁን ላይ እየተቀረፈ መሆኑን ይገልጻል።

የባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሃንሰ አያሌው የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መሻሻል ማሳየቱን ጠቅሰው፥ ህዳር ወር ላይ 25 ከመቶ እንዲሁም በታህሳስ ወር በ27 ከመቶ ማደጉን ያነሳሉ።

በባለስልጣኑ የተነሳው የውጭ ምንዛሪ ብድር ማጣት ችግር በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም ገልጸዋል።።

ከሁለቱ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የከተማዋን መሃል አካባቢ የውሃ እጥረት ችግር ይፈታል የተባለ አነስተኛ ስምንት የውሃ ፕሮጀክቶች ቁፋሮ በ80 ሚሊየን ብር ተከናውነዋል።

በለገሃር፣ ሽሮሜዳ፣ እንጦጦ ኪዳነምህረት፣ ሃና ማርያም፣ ኮተቤ፣ ቦሌ መድሃኒያለምና አቃቂ ሰረጤ ተብሎ በሚጠሩ አካባቢዎች የቁፋሮ ስራው ተጠናቋል።

ቁፋሮው ከተጠናቀቀ አንድ አመት ቢያልፈውም እስካሁን ወደ ስርጭት አለመግባቱን በስፍራው ባደረግነው ቅኝት ማረጋገጥ ችለናል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ በጉድጓዶቹ ውስጥ ከፍተኛ የኬሚካል ክምችት መኖሩ ስርጭት እንዳይጀምር ማድረጉን ገልጸዋል፤ ችግሩን ለመፍታትም ኬሚካሉን የሚያጣራ የማሽን ግዥ ለመፈጸም ሂደት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ።

አሁን ላይም አምስት ኩባንያዎች ማሽኑን ለማቅረብ እየተወዳደሩ ነው ተብሏል፤ ሂደቱ እንዳለቀም ኬሚካሉን በማጣራት የውሃ ስርጭት እጀምራለሁ ነው ያለው ባለስልጣኑ።

 

 


በታሪክ አዱኛ