ፈረንሳይ የሶሪያ መንግስት የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀሙ ከተረጋገጠ ጥቃት እንደምትፈጽም አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ የሶሪያ መንግስት የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች መጠቀሙን የሚያሳይ መረጃ ካገኘች ጥቃት እንደምትፈጽም አስታወቀች።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሃገራቸው የበሽር አላሳድ መንግስት በንጹሃን ላይ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች መጠቀሙን የሚያሳይ ትክክለኛ መረጃ ካገኘች ጥቃት ትፈጽማለች ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ የሶሪያ መንግስት ይህን ማድረጉን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ከተገኘባት ፓሪስ፥ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎቹ በሚገኙበት ቦታ ጥቃት እንደምትፈጽም ተናግረዋል።

ማክሮን በንግግራቸው የሶሪያ መንግስት ይህን ካደረገ ፈረንሳይ ያሰመረችውን ቀይ መስመር እንደመሻገር ይቆጠራልም ነው ያሉት።

ማክሮን በንግግራቸው የፈረንሳይ የደህንነት ሰዎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተረጋገጠ መረጃ አለማግኘታቸውንም አንስተዋል።

ይሁን እንጅ በሚደገው መጣራት የአላሳድ መንግስት የኬሚካል የጦር መሳሪያ መጠቀሙ ከተረጋገጠ፥ ፈረንሳይ መሳሪያዎቹ የሚገኙበት ቦታ ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፓሪሱ መግለጫቸው ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ያደረጉትን ንግግርም አንስተዋል።

በተጠናቀቀው 2017 በጉዳዩ ላይ ባደረጉት የስልክ ውይይት ሶሪያ ይህን የምታደርግ ከሆነ ቀዩን መስመር በመሻገር ህግ መጣሷን መናገራቸው ይታወሳል።

የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፥ የሶሪያ መንግስት የክሎሪን ጋዝ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተጠቀመ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ወር በሶሪያ ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉ አለም አቀፍ ተቋማት፥ የበሽር አላሳድ መንግስት በንጹሃን ላይ ኬሚካል የጦር መሳሪያዎችን እየተጠቀመ ነው በማለት ወቀሳ አቅርበዋል።

ምዕራባውያን ሃገራት ሶሪያ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ክምችት አላት በማለት ይወቅሳሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሶሪያ መንግስት የኬሚካል ጦር መሳሪያውን እንዲያስወግድ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ አቅርበዋል።

ይሁን እንጅ እስካሁን የኬሚካል የጦር መሳሪያ ማከማቻ ስፍራዎች ናቸው ተብለው ከሚታመኑት መካከል በተወሰኑት የሚገኙትን ብቻ ማስወገዱ ነው የሚነገረው።

 

 

 

ምንጭ፦ አር ቲ