የደቡብ ሱዳን መንግስት ለሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ተዘጋጅቷል- አምባሳደር ሞርጋን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መንግሥት ለሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሬክ ማቻር መካከል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈረምም በስምምነታቸው መቀጠል አልቻሉም።

በዚህም የተነሳ ደቡብ ሱዳናዊያን ሰላምና መረጋጋት ከራቃቸው ሰንብተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በገለልተኛ ወገን እንዲሁም በኢጋድ አደራዳሪነት ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢፈረሙም ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ድርድሩ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ አንደኛው በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት፤ ሁለተኛው ደግሞ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ነው።

የሀገሪቷን ሁኔታና የድርድሩን ሂደትና ግብ በማስመልከት በኢትዮጵያና በጅቡቲ የደቡብ ሱዳንን አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድና የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ ከሆኑት ጀምስ ፒ ሞርጋን እንደገለጹት፥ በአገሪቱ ያለውን ግጭት ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን መንግሥት ለመላው ተቃዋሚ የፖለቲካ አባላት የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ፍላጎት አለው።

ለችግሩ እልባት ለመስጠት መንግሥት የልዑካን ቡድኑን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁለተኛው ምዕራፍ የእርቅ መድረክ ላይ እየተሳተፈ ነውም ብለዋል።

“በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ለመስማማት መንግሥት ዝግጁ ነው፤ ሁሉም በዚህ እንዲስማማም ውይይቱ ተጀምሯል” ነው ያሉት አምባሳደሩ።

በአደራዳሪው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አማካኝነትም ችግሩን ለመፍታት የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ሀሳብ በመቅረቡ መንግሥት ይህን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

“ሁለት የተለያዩ ወታደራዊ ኃይል ያለው ሀገር የለም” ያሉት አምባሳደር ሞርጋን፥ ከሁሉም ወታደራዊ ቡድኖች የተውጣጣ አንድ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል ለማቋቋም መግባባቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

"ደቡብ ሱዳናዊያን ዴሞክራሲን ተርበዋል፤ መሪያቸውንም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም ይህን ለማድረግ መጀመሪያ በሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በዘላቂነት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በሀገሪቷ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ከኢጋድና ሌሎች ገለልተኛ ወገኖች የቀረበውን ሀሳብ መንግሥት እንደሚቀበልም አምባሳደር ሞርጋን ገልጸዋል።

ሙሉ በሙሉ ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነና የሕዝብ ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንደሚመሰረትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለድርድሩ እንደ ኢጋድ አባልነትም እንደ ጎረቤትም ላበረከተችው ትልቅ አስተዋጽኦ አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።

ደቡብ ሱዳናዊያን ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የጀመሩት ሁለተኛ ምዕራፍ ድርድር አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በተካሄደው ስምምነት ሁለቱ ወገኖች በሥልጣን ክፍፍል ላይ መስማማታቸው የሚታወስ ይታወሳል።

በዚህም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ቡድን 53 በመቶ የሚሆነውን የካቢኔ ወንበር፤ የዶክተር ሬክ ማቻር ቡድን ደግሞ 33 በመቶ እንዲይዝ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ