በሊቢያ ስደተኞችን የጫነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ተጋጭቶ 23 ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊቢያ ስደተኞችን የጫነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ተጋጭቶ 23 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

የጭነት ተሽከርካሪው በአብዛኛው ኤርትራውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞችን አሳፍሮ ከመዲናዋ በስተደቡብ አቅጣጫ ወደ ምትገኘው ባኒ ዋሊድ ከተማ እያመራ ነበር ተብሏል።

በተሽከርካሪው በወቅቱ ከ300 በላይ ጥገኝነት ፈላጊ ስደተኞች ተጭነው ነበር ነው የተባለው።

በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪም ወደ 100 በሚጠጉት ላይ ጉዳት ደርሷል።

የባኒ ዋሊድ ከተማ መዳረሻቸውን ጣሊያን ያደረጉ አፍሪካውያን ስደተኞች ለሚያደርጉት የባህር ጉዞ መነሻ በመሆን ታገለግላለች።

ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የሚመጡ ስደተኞችም በከተማዋ በመሰባሰብ በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በትናንሽ ጀልባዎች አስቸጋሪውን የባህር ላይ ጉዞ ያደርጋሉ።

ከሊቢያ በመነሳት ወደ አውሮፓ በሚደረግ የባህር ላይ ጉዞ በርካታ አፍሪካውያን ለህልፈት ይዳረጋሉ።

ከ10 ቀናት በፊት መዳረሻቸውን አውሮፓ ያደረጉ 90 ስደተኞች በሊቢያ የባህር ዳርቻዎች መስጠማቸው የሚታወስ ነው።

ከዚያ ቀደም ባለው ሳምንት ደግሞ 25 ስደተኞች በተመሳሳይ የጀልባ አደጋ ለህልፈት ተዳርገዋል።

ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም ጀምሮ እስካለፈው አመት ህዳር ወር ድረስ ደግሞ ወደ አውሮፓ በተደረገ የባህር ላይ ጉዞ፥ ከ33 ሺህ በላይ አፍሪካውያን የባህር ሲሳይ መሆናቸውን ከመንግስታቱ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

 

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ