ኩዌትና ጣሊያን ኢራቅን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ብድር ለመስጠት ቃል ገቡ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃገራት ኢራቅን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ብድር እና እርዳታ እንደሚሰጡ ቃል እየገቡ ነው።

አለም አቀፍ ለጋሽ ሃገራትና ባለሃብቶች ኢራቅን መልሶ ለመገንባት ሊደረግ ስለሚገባው ጥረት በኩዌት እየመከሩ ነው።

በመድረኩ ላይም የተለያዩ ሃገራት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት ለሚደረግው ጥረት አጋርነታቸውን እያሳዩ ነው።

የመድረኩ አስተናጋጅ ኩዌት ሃገሪቱን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር እንደምትሰጥ ቃል ገብታለች።

የኩዌቱ ኤሚር ሼክ ሳባህ አል አህመድ አል ጃባር አል ሳባህ፥ ሃገራቸው የባግዳድ ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያገግም ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

ከብድሩ ባለፈም ሃገራቸው በኢራቅ በሚደረጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና መሰል ዘርፎች እንደምትሳተፍም ተናግረዋል።

ለዚህም በኢንቨስትመንት መልክ ተጨማሪ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ ታደርጋለችም ነው ያሉት።

ከኩዌት ባለፈም ጣሊያን በጽንፈኛው አይ ኤስ ለፈራረሰችው ኢራቅ 321 ሚሊየን ዶላር ብድር እሰጣለሁ ብላለች።

የሃገሪቱ የልማት ትብብር ሃላፊ ጂዮርጂዮ ማራፖዲ እንዳሉት፥ ሃገራቸው ከብድሩ ባሻገር የ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ታደርጋለች።

ከዚህ ባሻገርም በሃገሪቱ ላለው ሰብዓዊ ቀውስ የ5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጸዋል።

ለሁለት አመት ያክል በጽንፈኛው አይ ኤስ 1/3 ግዛቷ ተይዞ የቆየው ኢራቅ በርካታ ጥንታዊ ቅርሶቿ ወድመውባታል።

አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም የሚታይባት ኢራቅ ወደ መልሶ ግንባታ ለመግባት እንቅስቃሴ ጀምራለች።

በኩዌት የተዘጋጀው መድረክም ይህን ጥረት ለማገዝና መወሰድ በሚገባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የሚመክር ነው።

 

 

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ