የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከዙማ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚባሉት የጉፕታ ቤተሰብ መኖሪያ ድንገተኛ ፍተሻ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚነገረው የህንዳውያኑ ጉፕታ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ማካሄዱ ተሰማ።

የሃገሪቱ ፖሊስ ፍተሻውን ያካሄደው የጉብታ ቤተሰብ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በጥቅማ ጥቅምና በሙስና ግንኙነት አላቸው በሚል መሆኑም ተሰምቷል።

በዚህም ከሶስቱ የጉፕታ ቤተሰብ ወንድማማቾች አንዱ በቁጥጥር ስር ውሏል ነው የተባለው።

ቀሪ ሁለቱ ወንድማማቾች ደግሞ እጃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የጉፕታ ቤተሰብ በሚል የሚታወቁት የህንድ ተወላጆች በደቡብ አፍሪካ ከፕሬዚዳንት ዙማ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል።

ይህን ግንኙነታቸውን በመጠቀምና በሀገሪቱ ፖሊቲካዊ ተጽዕኖን በመፍጠር በርካታ ሃብትና ንብረት አፍርተዋል በሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል።

ፕሬዚዳንት ዙማም ከሚታሙበት የሙስና ወንጀል ከጉፕታ ቤተሰብ ጋር ያላቸው ትስስር ዋነኛው ተደርጎ ይጠቀሳል።

ፕሬዚዳንት ዙማም ሆኑ የጉፕታ ወንድማማቾች ግን በመንግስት በኩል የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ያጣጥሉታል።

በተያያዘም ፕሬዚዳንት ዙማ በሰዓታት ውስጥ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ ምንም ያጠፋሁት ጥፋት ባለመኖሩ ስልጣኔን አለቅም ሲሉም ከሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

እርሳቸው በፓርቲያቸው የቀረበው ከስልጣን ይውረዱ ጥያቄ ምክንያት የሌለውና አግባብ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።

ከስልጣን እንድወርድ በቂ ምክንያት አልቀረበልኝም ያሉት ዙማ፥ ይህን ተከትሎም ከስልጣን እንዲወርዱ የሚያደርጋቸው ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ስልጣን አለቅም ማለታቸውን ተከትሎም የሀገሪቱ ፓርላማ በነገው እለት በፕሬዚዳንቱ ቆይታ ላይ የመተማመኛ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ