እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌና አሕመዲን ጀበልን ጨምሮ ይቅርታ የተደረገላቸውና ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ዛሬ ተለቀዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት በተከታታይ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሽብር እንዲሁም በሀይማኖት አክራሪነት ክስ የተመሰረተባቸው እና ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦች ላይ ክስ የማቋረጥ እና ይቅርታ የማድረግ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳረጋገጠውም ክሳቸው የተቋረጠላቸው እና ይቅርታ የተደረገላቸው ተጠርጣሪዎች እና ፍርደኞች ዛሬ በመለቀቅ ላይ ይገኛሉ።

እስካሁንም እስክንድ ነጋ እና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይን ጨምሮ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል፣ ካሊድ ኢብራሂም፣ አህመድ ሙስጠፋ እና መሐመድ አባተ ተለቀዋል።

በይቅርታ እና ክሳቸው ተቋርጦ ከተለቀቁ ግለሰቦች መካከልም ትናንት አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች ሰባት ተጠርጣሪዎች ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።