ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ሰላም በማስከበር ያስገኘችው ውጤት በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት እንዳሳደገው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ሰላም ማስከበር በመሰማራት ያስገኘችው ውጤት በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ሀብታሙ ጥላሁን ተናገሩ።

በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ረጅም አመታት ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ፥ በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን ሰፊ ስራን አከናውናለች።

በአሁኑ ወቅትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በመሆን፥ በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ ከ13 ሺህ የሚበልጡ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቷን አሰማርታ ሰራዊቱም ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ሀብታሙ ጥላሁን፥ ሰላም አስከባሪ ሃይሉ ያሳየው ህዝባዊነትና ተልዕኮውን የመፈፀም አቅሙ አሁንም ድረስ በተለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲቀርቡለት ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

ብርጋዴር ጀኔራል ሀብታሙ ሰላም አስከባሪ ሃይሉ በደቡብ ሱዳን አብየ ግዛት በመስፈር ግዳጁን በመወጣቱ የሁለቱ ሱዳን ህዝቦች የጠበቁትን እንዳገኙም ነው የሚናገሩት።

አሁን ላይም ፖለቲካዊ መፍትሄ ያላገኘው የደቡብ ሱዳን ግጭት ከዚህ የባሰ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የኢፌዴሪ ሰላም አስከባሪ ሃይል በጁባ ተሰማርቶ ግዳጁን እየተወጣ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ የሃገሪቱ አለመረጋጋት ለመፍታት በኢጋድ በኩል ከምታደርገው ጥረት ባሻገርም፥ ሰራዊቱ ከሌሎች ሀገራት ወታደሮች ጋር በመሆን በሃገሪቱ ሰላም የማስከበር ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰራዊቱም የደቡብ ሱዳን ንፁሃን ዜጎች የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸዉ የመከላከል ስራዎቹን እየፈፀመ ይገኛልም ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ መንግስት አልባ ሆና ለበርካታ አመት የዘለቀችው ሶማሊያን አንፃራዊ ሰላም እንድትቀናጅ ያደረገችው ጥረት ከፍተኛ መሆኑም ይነገራል።

በተለይም ለምስራቅ አፍሪካና ለአለም ስጋት ሆኖ የቆየው አልሸባብ አቅሙ እንዲዳከም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያደረገው ጥረት ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳል።

ብርጋዴር ጀኔራል ሀብታሙ ሰላም አስከባሪ ሀይሉ የነበሩ ግጭቶች እንዳይቀጥሉ ከማድረግ፣ የሚደረጉ የሰላም መፍትሄዎች በግጭት ምክንያት እንዳይደናቀፉ ከማድረግና ንፁሃን ዜጎችን ከመጠበቅ አንጻር አመርቂ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

ጣቢያችን ያናገራቸው ምሁራን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም እንዲህ ያሉ ተግባራትን መከወኗ አብሮ ለመልማት ካላት ፍላጎት አንጻር የሚመነጭ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ ኢትዮጵያ ከቀጠናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው ኢኮኖሚዊና የልማት መስኮች ትስስር በአካባቢው ያለው ቀውስ እልባት ማግኘት ወሳኝነት አለው።

ሃገሪቱ አሁን ያላትን አለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግም የስልጠና ማዕከል ከፍታለች።

የስልጠና ማዕከሉ ከሃገሪቱ ሰራዊት አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በግጭት አፈታትና አያያዝ ዙሪያ ስልጠናዎችን ይሰጣል።

 

 


በተመስገን እንዳለ