ብሪታንያ በሩሲያ ሰላይ ላይ በተፈፀመ የመርዝ ጥቃት ዙሪያ ሞስኮ ማብራሪያ እድትሰጣት አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሪታንያ በሀገሯ የሚገኝ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይና የልጁ ጥቃት በሩሲያ የተሰራ የነርቭ መርዝ ለምን ጥቅም ላይ እንደዋለ ሞስኮ ማብራሪያ እንድተሰጥ የመጨረሻ ቀነ ገደብ አስቀምጣለች።

በብሪታንያ የሚኖረው የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ ሰርጌ ስክሪፓል እና ሴት ልጁ ላይ በሩሲያ የተሰራ ነርቭን የሚያጠቃ መርዛማ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ይታወሳል።

የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ፥ ባሳለፍነው እሁድ በዊልሻየር ሳሊስበሪ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ተያይዞ ዋነኛዋ ተጠያቂ ሩሲያ ልትሆን እንደምትችል አስታውቀዋል።

ሩሲያ በበኩሏ እየቀረበባት ያለው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ስትል አስተባብላለች።

የብሪታንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣሉ የተባለ ሲሆን፥ የብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አምበር ሩድ ስብሰባውን እንደሚመሩትም ተነግሯል።

ባሳለፍነው እሁድ በ66 ዓመቱ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ ሰርጌ ስክሪፓል እና የ33 ዓመቷ ሴት ልጁ ዩሊያ ላይ በዊልሻየር ሳሊስበሪ ከተማ በሚገኝ የባህር ዳርቻ ላይ ነው የነርቭ ጥቃቱ የተፈፀመው።

አባትና ልጅ በጥቃቱ ክፉኛ የተገዱ እና አስጊ ደረጃ ላይ እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፥ አሁን ላይ ግን በተረጋጋ ሁኔታ በሆስፒታል ሆነው ህከምናቸውን እየተከታተሉ ነው ተብሏል።

የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በጥቃቱ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፥ ለጥቃቱ ጥቅም ላይ የወላው መርዝ “ኖቪቾክ” መሆኑን እና መርዙ በሩሲያ ጦር የተሰራ ነርቭን የሚጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ሜይ፥ “ይህ ጥቃት በቀጥታ በሩሲያ አማካኝነት የተፈፀመ አሊያም መርዙ ከሩሲያ እጅ አፈትልኮ ወጥቶ በሌሎች እጅ ከገባ በኋላ ጥቅም ላይ ሳየውል አልቀረም” ብለዋል።

የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሁለቱ መላ ምቶች ትክክለኛው የቱ ነው የሚለው ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው በሀገሪቱ ለሚገኙት የሩሲያ አምባሳደር ጥሪ ማቅረቡንም አስተውቀዋል።

ሜይ፥ “እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ አስተማማኝ መልስ የማይሰጥበት ከሆነ ሩሲያ ህግ ወጥ ተግባር ፈፅማለች የሚል ድምደሜ ላይ እንደርሳለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለውም፥ ብሪታንያ ከዚህ ቀደሙ በበለጠ በሩሲያ ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗንም የገለጹ ሲሆን፥ እርምጃዎቹም በነገው እለት የሚታወቁ መሆኑን ገልፀዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በጉዳዩ ዙሪያ ከብሪታንያው አቻቸው ቦሪስ ጆንሰን ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት አሜሪካ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ሩሲያን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ወስጥ ብሪታንያን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

ምንጭ፦ www.bbc.com