በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 143 ሚሊየን ሰዎች ለስደት ይዳረጋሉ - አለም ባንክ

አዲሰ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2010 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ባለበት መልኩ ከቀጠለ በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ 143 ሚሊየን ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል ሲል የዓለም ባንክ አስጠንቅቋል።

የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንዳመለከተው ከሆነ በአየር ንብረት ለውጥ በአዳጊ ሀገራት የሚገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ የሚሆኑት ዜጎች እንደሆኑ አመልክቷል።

ድርቅ፣ የምርት መቀነስ፣ የውቂያኖስ የውሃ መጠን መጨመር ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት ይሆናል ሲል ነው ያስቀመጠው።

በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥም በዚህ ምክንያት ለመፈናቀል የሚገደዱ ሰዎች ቁጥር 143 ሚሊየን ይደርሳልም ብሏል።

በተለይም ከሰሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ክፍል እስከ 86 ሚሊየን የሚደርሱ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉበት ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል።

የዓለም የእየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትለው የበካይ ጋዞች ልቀትን መቀነስና ዘላቂ ልማትን የሚያመጡ ስልቶችን በተጨባጭ መተግበር ካልተቻለ የለውጡ ተፅዕኖ ከዚህም በከፋ ሁኔታ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቋል ባንኩ።

ምንጭ፦ ሲኤንኤን