ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ ለከተሞች ልማት የሚውል የ600 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ ለከተማ ልማት ፕሮጀክት የሚያግዝ የ600 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድርና ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ ከተሞች የአስተዳደር አካላትን አቅም ለማሳደግ፣ መሰረተ ልማት ለማስፋፋትና የከተሞችን ልማት ለማፋጠን ነው።

ስምምነቱ የ400 ሚሊየን ዶላር ብድር እና 200 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ በኢትዮጵያ የከተሞችን ልማት ለማፋጠን በድጋፍ የተሰጠ ነው።

የፋይናንስ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ፣ በዓለም ባንክ በኩል የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ተፈራርመዋል።

ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮግራም ሲፈፀም በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 117 ከተሞች የሚኖሩ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፥ የገንዘብ ስምምነቱ በአገሪቷ የከተሞችን አስተዳደራዊ አቅም በማጎልበትና መሰረተ ልማት በማስፋፋት ልማትና እድገታቸውን ያፋጥናል ብለዋል።

ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗን ጠቁመው፥ የተሰጠው ድጋፍ ለስራ እድል ፈጠራና ድህነትን ለመቀነስ ስለሚያግዝ ለታለመለት ሥራ እንዲውል አሳስበዋል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው፥ ገንዘቡ መንግስት በከተሞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገራት የኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በከተሞች የሚስተዋለው የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎቶችና የስራ እድሎች አቅርቦት ያለመመጣጠን ችግሮች ለመፍታት የዓለም ባንክ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ