የአሜሪካ መጤ ተምች በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል

አዲሰ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2010 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) በመስኖ ልማት ላይ በመጠኑ እየታየ ያለው አሜሪካ መጤ ተምች በበልግም ሆነ በክረምት ሰብል ላይ ጉዳይ እንዳያደርስ ሁሉም ክልሎች መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፎል አርሚ ወርም ወይም አሜሪካ መጤ ተምች ተብሎ የሚጠራው ተባይ በሀገሪቱ ባለፈው አመት ተከስቶ ነበር።

ይህ ተባይ 80 በመቶ የሚሆነውን አዝርእርት ማጥቃት የሚችል ሲሆን፥ በሀገራችን እስካሁን ጉዳት ያደረሰው የበቆሎ ምርት ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

ለዚህም መጀመሪያ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ ሾሻ ቀበሌ በመስመር በተዘራ በቆሎ ላይ የታየው ይህ ተባይ፥ በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻጉል፣ አማራ አና ትግራይ ክልልን ጊዜ ሳይወስድ መዛመት ችሏል።

በዚህም ከ300 እስክ 500 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ይህ አደገኛ ተባይ በባለፈው አመት በመህር የእርሻ ወቅት ከተዘራው 2 ሚሊየን ሄክታር በቆሎ 20 በመቶ የሚሆነው ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ተገልጿል።

የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢያሱ አብርሀ፥ ከአመራር ጀምሮ ባለሞያው እና አርሶ አደሩ ባደረጉት ርብርብ የጉዳቱን መጠን በ5 በመቶ መቀነስ ለሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ መሆን የሚችል ተግባር መከናወኑን ላፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በባለፈው አመት የተከሰተውን ይህ ተባይ 47 በመቶ የሚሆነው በኬሚካል እና 53 በመቶውን ደግሞ በአርሶ አደሩ ርብርብ ማጥፋት እንደተቻለ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ለዚህም አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚያመርተው እና በሚጠቀመው በቆሎ ላይ ጉዳት በማድረስ እንዳያጠፋው ለማድረግ ሰፊ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ የተለያዩ መስኖ ልማቶች ላይ የጉዳቱ መጠን የሚለያይ የአሜሪካ መጤ ተምች መከሰቱ ተጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልል እና ደቡብ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች ስለጉዳት በሰጡት አስተያየት፥ ተባዩ በበቆሎ ምርታቸው ላይ ጉዳት ማድረሱ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል መሰኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የመስኖ ልማት ኤክስቴንሽን ስራ ሂደት መሪ አቶ አብዲ ኢተፋ፥ እሰከ ዛሬ ባለው መረጃ በክልሉ በ10 ዞኖች ላይ ተባዩ እንደተከሰተ ገልፀዋል።

ይህን ተባይ የመከላከል ስራም በአብዛኛው በአርሶ አደሩ እጅ ለቀማ እየተካሄደ እንደሚገኝ እና ተባዩ በዝቶ በሚታይባቸው አካባቢዎች ብቻ ኬሚካል እንሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል ሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳሬክተር አቶ ተሰማ ዲኖሬ በበኩላቸው፥ በክልሉ በመስኖ ከለማው 455 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተሰራው ሰፊ የመከላከል ስራ በ217ቱ ላይ ብቻ የተከሰተ ሲሆን፥ ለዚህም የተባይ ቁጥጥሩ በሁሉም ማሳዎች ላይ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኢያሱ ከየካቲት 15 እስክ 28 2010 ድረስ ባለው መረጃ፥ በሀገሪቱ በሚገኙ 26 ዞኖች፣ 104 ወረዳ በመስኖ እየለማ በሚገኝ ከ15ሺ ሄክታር መሬት ላይ በተዘራ የበቆሎ ምርት ላይ መከሰቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በስርጭት ደረጃ በስፋት የማይታይ በመሆኑ በመከላከሉ ላይ አርሶ አደሩ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የገለፁት።

እንዲሁም በኬሚካል ዝግጅት በኩል አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 100 ሺህ ሊትር ኬሚካል እንዲያዘጋጅ መደረጉን አስታውቀዋል።

ይህ አደገኛ ተባይ በ2 ሚሊየን መሬት ላይ የሚለማውን ከ80 እስከ 83 ሚሊየን ኩንታል የበቆሎ ምርት እንዳያሳጣን በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

ለዚህም ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ከስልጠና ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በባለፈው አመት በተገኘው ተሞክሮ መሰረት አርሶ አደሩ በየቀኑ ማሳውን በመመልከት ተባዩ እንዳይስፋፋ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።

ከዚህ ተባይ ተፅዕኖ ውጪ የሆነ ክልል አለመኖሩን የገለፁት ሚንስትሩ፥ ጉዳቱ ወደ በልግ እና ክረምት እርሻ እንዳይዛመት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

 

 

 

ሰርካለም ጌታቸው