ማይክ ፖምፒዮ አሜሪካ በኢራን ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንደምትጥል ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ሃገራቸው በኢራን ላይ በአይነትም ሆነ በይዘቱ ጠንካራ የሆነ ማዕቀብ እንደምትጥል ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው፥ ዋሽንግተን ቴህራንን በተመለከተ የምትከተለውን ተለዋጭ እቅድ ለሃገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ይፋ አድርገዋል።

በንግግራቸውም ዋሽንግተን በቴህራን ላይ በታሪክ ጠንካራውን ማዕቀብ እንደምትጥል ገልጸዋል።

ፖምፒዮ በንግግራቸው ከሃገሪቱ መከላከያ እና አጋር አካላት ጋር የኢራንን አግባብ ያልሆነ አካሄድ ለመግታት በቅርበት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈጸምም ሆነ ለመደራደርም ቴህራን 12 ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባት አንስተዋል።

በሶሪያ ያላትን ጦር ሙሉ በሙሉ ማስወጣትና በየመን ለአማጽያን የምታደርገውን ድጋፍ ማቋረጥም ከቴህራን ይጠበቃልም ነው ያሉት።

ማንነታቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ዲፕሎማት በበኩላቸው የኢራን ባለስልጣናት የአሁኑን የአሜሪካን ዝግጅት በቸልታ እንደማያዩት ጠቅሰዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸውን ከኢራን ጋር ከገባችበት የኒውክሌር ስምምነት ከሁለት ሳምንት በፊት ማስወጣታቸው የሚታወስ ነው።

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ