Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝብን ወደ አንድ የሚያቀራርቡ አማራጮችን ሊያቀርቡ ይገባል – የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝብን ከመነጣጠል ይልቅ ወደ አንድ የሚያቀራርቡ አማራጮችን ሊያቀርቡ እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የጠበበውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ በሽብር ተፈርጀው የነበሩና በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖች እና አክቲቪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉትም ሆነ ከውጭ የገቡት ፓርቲዎች ተሳትፏቸው በሚጎላበት ሁኔታ ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፤ የተጀመረው ጥረት ተስፋ ቢያሳይም ከፈተናዎች ግን አልፀዳም።

በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለች ሀገር ውስጥ የሚያጋጥሙ ተጠባቂ ችግሮችን በመጠምዘዝ ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሞከሩ ቡድኖችም አልጠፉም።

ተቃውሞን በሀይል እና ጉዳት በሚያደርስ መልኩ እንዲከወን የመረጡ ቡድኖችም የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ስጋት ውስጥ ጥለውታል።

በእነዚህ ሀይሎች ላይ እርምጃ ወስዶ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ የሚገባው መንግስትም የበዛ ትዕግስት ማሳየቱ ነገሮችን እንዳባባሳቸው አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አሁን ላይ ሀገሪቱ የፖለቲካ መንታ መንገድ ላይ እንድትሆን መሰረታዊ ምክንያቱ የመንግስት ህግና ስርዓትን በአግባቡ አለማስከበር መሆኑን ያምናል።

የአብን ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ማንኛውም አይነት ተቃውሞ እና የሀሳብ ልዩነት በሰለጠነ መንገድ መካሄድ እንዳለበት ይገልጻሉ።

ከ180 በላይ ህዝባዊ ውይይቶችን ያካሄደውና በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉት የሚገልፀው አብን፥ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አባላቶቹ፣ ደጋፊዎቹ እና መላው የአማራ ህዝብ የሰለጠነ ፖለቲካዊ እሳቤ እንዲይዙ እየሰራሁ ነው ይላል።

ሊቀመንበሩ ዶክተር ደሳለኝ እንደሚሉትም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው ህግና ስርአትን እንዲያከብሩ ሊሰሩ ይገባል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው አረና ፓርቲም መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ትልቁን ስራ እንደሚሰራ በመጥቀስ፥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንኑ ስራ የማገዝ ግዴታ አለባቸው ይላል።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ያለሰላም የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሆነ ህዝብ እና ሀገር አይኖሩምና ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለምንም ልዩነት ቅድሚያ ለሰላም መስራት አለባቸው ብለዋል።

ፓርቲዎች ህዝብን ከሚያራርቅ ነገር ይልቅ የሚያቀራርቡ አማራጮችን ማቅረብ አለባቸውም ነው የሚሉት ሊቀ መንበሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና በህዝብ ደህንነት እና መረጋጋት ላይ የተመሰረተ ነው የሚሉት አቶ አብርሃ፥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎቻቸውን ሊገስፁ ከፍ ሲልም እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ነው ያሉት።

የተለያዩ ፓርቲዎች ውህድ የሆነው መድረክ በበኩሉ 12 አባላት ያሉት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያለው ሲሆን፥ ኮሚቴው በየሁለት ሳምንቱ እየተገናኘ በድርጅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል።

ፓርቲው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ለማስቆም ህዝቡ የሚተማመንበትና ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለይም ተቀባይነት ያላቸውን ያካተተ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት እንዲመሰረት መጠየቁም ይታወሳል።

ጥያቄው እስካሁን ተቀባይነት ባያገኝም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ብቻ ባለመሆኑ፥ መድረክም አባላት እና ደጋፊዎቹ ወደ ግጭት ከሚከቱ ነገሮች እንዲቆጠቡ እየሰራ መሆኑን ነው የፓርቲው ፀሃፊ አቶ ደስታ ዲንቃ የሚናገሩት።

ሶስቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውህደት፣ ጥምረት እና ግንባር በመፍጠር ጉዳይ ላይ ዝግጁ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

ለቀጣዩ ምርጫ እየተዘጋጀሁ ነው ያለው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ፥ የመሬት እና ንግድ ፖሊሲ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የትምህርት፣ ማህበራዊ ልማት እና ሌሎች የመወዳደሪያ አማራጮችን ማዘጋጀቱንም ነው ሊቀመንበሩ ያነሱት።

አረናም ምንም እንኳን ተዘዋውሮ የመቀስቀስ ችግር ቢገጥመውም ለምርጫው እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ሊቀመንበሩ አቶ አብርሃ ይናገራሉ።

መድረክም እንዲሁ በምርጫው የሚወዳደሩ እጩዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የፓርቲው ፀሃፊ አቶ ደስታ ገልጸዋል።

የፓርቲ አመራሮቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ መንግስት ህግና ስርአትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.